#FastMereja I በአፋር ክልል ኤሬብቲ ወረዳ ልዩ ስሙ “ሔርቶ በህሪ” በተባለ አካባቢ፣ ከጅቡቲ ወደ መቐለ ሲጓዝ የነበረ አሽከርካሪ በታጠቁ ግለሰቦች በተከፈተበት ተኩስ ሕይወቱ ማለፉን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ። ጥቃቱን ከፈጸሙት ሁለት ግለሰቦች መካከል አንዱ ቆስሎ በቁጥጥር ሥር ሲውል፣ ሁለተኛው ተጠርጣሪ ወደ ጫካ በመግባቱ ፍለጋ እየተካሄደበት ይገኛል።
ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:30 ገደማ፣ አሽከርካሪ አቶ ጥጋቡ ለገሰ ተሰማ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮ3-A35438/94911 ኢት የሆነ ከባድ መኪና በመንዳት ከጅቡቲ-ሰርዶ መንገድ ወደ መቐለ በመጓዝ ላይ ነበሩ። ተሽከርካሪው አፍዴራ ሲረባን አልፎ ኤሬብቲ ወረዳ ሲደርስ፣ ሁለት የታጠቁ ግለሰቦች መኪናውን በማስቆም በአሽከርካሪው ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ተረጋግጧል።
በደረሰው ጥቆማ መሠረት የጸጥታ አካላት በፍጥነት ቦታው ላይ የደረሱ ሲሆን፣ አንደኛው ተጠርጣሪ በግራ እግሩ ላይ በደረሰበት የተኩስ ቁስል ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውሏል። ሁለተኛው ግለሰብ የፖሊስ ተሽከርካሪን ከርቀት በማየቱ ወደ ጫካ ውስጥ በመግባት ለጊዜው የተሰወረ ቢሆንም፣ የፖሊስ አባላትና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል አሁንም በጫካው ውስጥ መጠነ ሰፊ አሰሳ እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ ያልተለመደ ያለውን ይህን አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ፣ ለተፈጠረው ክስተት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ በክልሉ ስም ይቅርታ ጠይቋል። ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ በሕግ እንደሚጠየቅና ያመለጠውን ግለሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ አድኖ ለሕግ ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል።
Source: FastMereja









No comments yet.