🙏
በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡
አባታቸው ጸጋ ዘአብና እናታቸው እግዚእ ኃረያ ፍሥሐ ጽዮን ብለው ሰየሟቸው፡፡ በአንድ ወቅት ታዳጊው ፍሥሐ ጽዮን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ጌታችን ተገልጦ ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሳደረባቸው፡፡ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ለስብከተ ወንጌል እንደሚልካቸውም አስረዳቸው፡፡ በተወለዱ በ15 ዓመታቸው መዓርገ ዲቊናን፣ በ22 ዓመታቸው ደግሞ መዓርገ ቅስናን ከግብጻዊው ጳጳስ አባ ቄርሎስ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባል፣ ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደሆነ አበሠራቸው፡፡
ወላጆቻቸው ካረፉ በኋላም ንብረታቸውን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ወጡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም ለ12 ዓመታት ተቀምጠው ሲወርዱ ገመዱ ቢበጠስ ስድስት ክንፍ አውጥተው በረዋል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ በርካታ አሕዛብን አጥምቀዋል፤ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡ በደብረ ሊባኖስ ገዳም አስቦ ዋሻ በዙሪያቸው ስምንት ጦሮች ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማምና ሞት በማሰብ ሌሊትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾምና በጸሎት ሲጋደሉ፤ ከመቆም ብዛት አንድ እግራቸው ተሰብራል፡፡
ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላም ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነትን ለምነዋል፡፡ ከዚህ ዓለም ድካም በሚያርፉበት ቀንም ጌታችን ከእናቱ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከወዳጆቹ ጋር መጥቶ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡
የጻድቁን ቃል ኪዳን ያመኑ ገዳማውያን እንደሳቸው ሁሉ ዓለምን ንቀው በተጋድሎ ይኖራሉና ከበረከታቸው እንድንሳተፍ ገዳማቸውን እየደገፍን በዓታቸውን እያጸናን ከበረከታቸው እንካፈል፡፡
ድጋፍ ለማድረግ፦ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444
Source: GetuTemesgen









No comments yet.