ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታልን ጎበኙ

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል ተገኝተው በኢትዮጵያዊያንና በውጭ ሀገር ስፔሻሊስቶች እየተከናወነ በሚገኘው የልብ ህሙማን ህፃናት የነፃ ቀዶ ጥገና አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ህፃናትን ጎብኝተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት ሆስፒታሉ እያከናወነ ያለውን ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎትና የበጎ አድራጎት ሥራ አድንቀው በኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፉ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ጠቁመዋል።

ለሕክምናው ቡድን አገልግሎት “Heart to Heart Children’s Aid” የተሰኘው ፋውንዴሽን ካሰባሰበው የእርዳታ ገንዘብ እና Ethio-Istanbul General Hospital ባደረገው ሙሉ የሆስፒታል አገልግሎትና የባለሙያዎች አቅርቦት በሚያደርጉት ድጋፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ሲሆን፣ በፕሮፌሰር ሳሻ የሚመራው የጣሊያኑ የ”ፔድሬ ፓዮ” የሕክምና ቡድንም በሥፍራው ተገኝቶ ከኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታል ባለሙያዎች ጋር በመዋሀድ እየሰጠ ባለው አገልግሎት በ12 ቀናት ውስጥ ብቻ በአዲስ አበባ 58 በጅግጅጋ 16 በድምሩ የ74 ሕፃናት የልብ ቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

​የሆስፒታሉ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃን ተድላ እንደገለጹት፣ ኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል አሁን የተሰሩትን 74 ህፃናት ሳይጨምር ባለፉት ሁለት ዓመታት ለ114 ሕፃናት በብር 120,000,000.00 (አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ብር) በሚገመት ወጪ ነፃ ሕክምና ሰጥቷል።
ሆስፒታሉ ከተመሰረተ ሦስት ዓመት ቢሆነውም፣ ከ86 በላይ የሰብስፔሻሊስት ዶክተሮችን በመያዝ ውስብስብ የልብ፣ የካንሰር፣ የደም ስር የጭንቅላት የህብለሰረስና የአጥንት ቀዶ ጥገና ህክምናና በሌሎችም አገልግሎቶች ላይ ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

​አቶ ብርሃን አክለውም፣ ሆስፒታሉን ለማቋቋም ያነሳሳቸው በራሳቸው ላይ የደረሰ የሕክምና እንግልትና ዜጎች ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር ሄደው የሚደርስባቸውን የገንዘብ ወጪና የሞራል ጉዳት ለማስቀረት ካላቸው ራዕይ መሆኑን በመግለፅ አገልግሎቱን ከዚህ በተሻለ በስፋት ለመስጠት እንዲያስችላቸው ላቀረቡት የቦታ ጥያቄ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥላቸው አሳስበዋል።

​ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በንግግራቸው፣ “ያስተማረንን ሕዝብ ማስታወስ ትልቅ በረከት ነው” በማለት በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንዲህ ያሉ ለትርፍ ብቻ ታስበው ሳይሆን ለመልካም አገልግሎት የተቋቋሙ የላቁ የሕክምና ተቋማት መኖራቸው ዜጎች ወደ ውጭ በመሄድ ከሚያወጡት ከፍተኛ ወጪና ከሚደርስባቸው እንግልት እንደሚታደጋቸውም ገልጸዋል።

​በተያያዘም ክቡር ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ለሕክምና ቡድኑ ባስተላለፉት የምስጋና መልእክት፣ በሕፃናቱና በቤተሰቦቻቸው ላይ የታየውን ደስታ “የተስፋ ብርሃን” በማለት ገልጸውታል። በተለይም የሕክምና ቡድኑ ወደ ጅግጅጋ በመጓዝ አገልግሎት መስጠቱ የሁለቱን ሀገራት (ኢትዮጵያና ጣሊያን) ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።

በዕለቱ ምስክርነታቸውን የሰጡ ወላጆች፣ የሕክምናውን ወጪ በመሸፈን ልጆቻቸው ማሳከም ባለመቻላቸው ለዓመታት ሲሰቃዩ መቆየታቸውን ገልፀው አሁን ባገኙት ነፃ የልብ ቀዶ ጥገና ልጆቻቸው ዳግም ሕይወት ማግኘታቸውን በደስታና በምርቃት ገልጸዋል።

ይህ የህፃናት ነፃ የልብ ሕክምና አገልግሎት በቀጣይነት ወደ ኦሮሚያ፣ አማራ፥ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ደቡብና ሌሎችም ክልሎች በመጓዝ ቀሪዎቹን ሕፃናት ለማከም ዕቅድ መያዙን አቶ ብርሃን ተድላ ገልፀው ለዚህ ዘመቻ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦና ትብብር ላደረጉት ለጤና ሚኒስቴር፣ ለጉምሩክ ኮሚሽን፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለስካይላይት ሆቴል፣ ለኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንና ለሌሎችም በዘመቻው ለተሳተፉ የህክምና ተቋማት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ በጎ አድራጊዎችና ለፋውንዴሽኑ የቦርድ አባላት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2