በዋስትና ከመፈታት አኳያ አዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ ያመጣቸው አዳዲስ ነገሮች መካከል:-

- Advertisement -
Sidebar AD

By Hailu Hasena (Legal Advocate)

1. “ያለ ዋስትና መለቀቅ (Release without bail/unconditional release)” የተሰኘ አዲስ ድንጋጌ አምጥቷል::

በዚህ ድንጋጌ መሠረት ተጠርጣሪው የተጠረጠበትን ወንጀል ስለመፈጸሙ ወይም የተባለው ወንጀል ስለመፈጸሙ አጠራጣሪ (doubtful) በሆነ ጊዜ የወንጀል ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤትም ሆነ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት ተጠርጣሪውን ያለ ዋስትና እንዲሁ እንዲለቁት ይገደዳሉ:: አንቀጽ 118(4)፣ 137(2)

*በቀድሞው የወ/መሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 59(1) እና 93 መሠረት የጊዜ ቀጠሮ እና የቀዳሚ ምርመራ ፍ/ቤቶች ተጠርጣሪው ወንጀል ስለመፈጸሙም ሆነ ወንጀሉ ራሱ ስለመፈጸሙ ቢጠራጠሩም ስንኳ ተጠርጣሪውን የግድ ዋስትና እንዲያስይዝ ወይም በማረፊያ ቤት እንዲቆይ እንዲያዙ ይገደዱ ነበር:: በአዲሱ መድብለ ሕግ ያ አሠራር ተሽሯል::

*ይህ ድንጋጌ በተለይ ለሚታፈሱ ወይም በመመሳጠር በፍ/ብሔር ወይም ወንጀል ባልሆነ ጉዳይ ለሚታሰሩ ሰዎች ይህ ትልቅ የሕግ ጥበቃ የሚያደርግ ነው::

*ስለዚህ የተያዙ ሰዎች የሚለቀቁባቸው መንገዶች እነዚህ ናቸው—ያለ ዋስትና መለቀቅ፣ ያለ ገደብ መለቀቅ፣ በራስ ዋስትና መለቀቅ፣ በንብረት ዋስትና መለቀቅ፣ በሰው ዋስትና፣ በገንዘብ ዋስትና መለቀቅ፣ በተጨማሪ ዋስትና መለቀቅ::

*ስለሆነም ከእንግዲህ የጠበቆች ሥራ የታሰረን ሰው በዋስትና ማስፈታት ብቻ ሳይሆን ያለ ዋስትና ማስፈታትንም ይጨምራል::

*Note: በፍ/ቤት መደበኛ ክስ (charge) የተከፈተ ከሆነ ያለ ዋስትና የመለቀቅ ጉዳይ አይነሣም::

2. በሕግ ዋስትና የሚያስከለክሉ ወንጀሎች (non-bailable crimes)
* በሞት የሚያስቀጡ ወንጀሎች፣ ወይም
* በ ≥15 ዓመት ጽኑ እሥራት የሚያስቀጡ ሰው የሞተባቸው ወንጀሎች ብቻ እንዲሆኑ የተደነገገ ስለሆነ በእንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች ውጭ ያሉ ወንጀሎች በሙሉ በሕግ ዋስትና የማያስከለክሉ ወንጀሎች (bailable crimes) ሆነዋል:: አንቀጽ 138(2,3)

ስለሆነም:-
➡️ስለሆነም በሕግ ዋስትናን በማይከለከልባቸው ወንጀሎች በመሉ ተጠርጣሪዎች/ተከሳሾች በዋስትና የመለቀቅ መብት አለው::

➡️በዕድሜ ልክ ወይም የጽኑ እሥራት ጣሪያ በሆነው በ25 ጽኑ እሥራት የሚያስቀጣ ወንጀል ብቻውን ዋስትናን አያስከለክልም::

➡️በማንኛውም የሙስና ወንጀል የተጠረጠረ/የተከሰሰ ሰው በሕግ ዋስትናን አይከለከልም—all corruption crimes have become bailable.

ከዚህ ቀደም በዐዋጅ ቁ. 434/1997 (በዐዋጅ ቁ. 882/2007 እንደተሻሻለ) አንቀጽ 4(1) መሠረት “ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተከሰሰ ሰው በዋስትና አይለቀቅም በማለት ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጡትን ለይቶ non-bailable corruption crimes ተደርጎ የነበረው ድንጋጌ ቀሪ (abolished) ተደርጎአል::

➡️በአደገኛ ቦዘኔነት ዐዋጅ ቁጥር 384/96 አንቀጽ 6(3) “በአደገኛ ቦዘኔነት ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስትና አይለቀቅም:” ተብሎ በወንጀል ዓይነት ዋስትና ይከለከል የነበረው (categorical bail denial) ዘፈቀዳዊ ነው ተብሎ በዚህ ዐዋጅ ተሽሮአል::

➡️በሕግ ዋስትና የማያስከለክሉ ወንጀሎችን (bailable crimes) አስመልክቶ ዋስትና መብት (right) ሲሆን ዋስትና ሊከለከልም ሊፈቀድም የሚችለው በዳኞች ፍቅድ ሥልጣን (judicial discretion) ነው::

ፍቅድ ሥልጣኑ የሚመራባቸው መርኆዎችም ደግሞ “ዳኛው ተጠርጣሪውን/ተከሳሹን በዋስትና ይለቃል የሚል ግምት (presumption of release on bail) ይወሰዳል:”፤ “ዋስትናን በሁኔታ የሚያስከለክሉ ሁኔታዎችም አይኖሩም: ተብሎ ይገመታል::”

“ዋስትናን ለመከልከል የሚያበቁ ልዩ ሁኔታዎች በጠባቡ እና ለተከሳሽ/ተጠርጣሪ በሚጠቅም መልኩ ይተረጎማሉ:” የሚሉ ናቸው—ከተመድ የሰብኣዊ መብቶች የዋስትና መብት ትርጉም አኳያ::

ለምሳሌ:- ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጣ ሌላ ወንጀል ይፈጽማል ወይም ማስረጃ ያጠፋል ወይም በተፈለገ ጊዜ አይቀርብም ወይም ቋም አድራሻ የለውም ወይም መውጣቱ ለኅ/ሰቡ ደኅንነት ያሰጋል ወይም የዋስትና ግዴታውን አይወጣም ወዘተ. የሚል ግምት አይያዝም::

ስለሆነም መርማሪ ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ እነዚህን መርኀዊ ግምቶች ለማስተባበልና ለመሠረታዊ መብቶች (የነጻነት መብት፣ ንጹሕ ሆኖ የመገመት መብት) የሥነ ሥርዓታዊ ጥበቃ የሆነውን የዋስትና መብት ለመቃወም ሕጋዊ፣ በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ያለ መሆኑን በቂ ማስረጃ በማቅረብ ማስረዳት ይኖርበታል::

3. የድኅረ ጥፋተኝነት ፍርድ ዋስትና (Post-conviction bail) የተሰኘ አዲስ ድንጋጌ አምጥቷል::
አንቀጽ 301(2)

ይህ ድንጋጌ ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ከተፈረደበት በኋላ የቅጣት ውሳኔ እስኪተላለፍበት ድረስ ባለው ጊዜ በዋስትና እንዲቆይ የሚያደርግ ነው::
ይሁንና ይህ ዋስትና የሚሠራው ወንጀሉ በመቀጮ ብቻ የሚያስቀጣ ሲሆን ነው::

እንደሚታወቀው በነባሩ የወ/ሕ/ሥ/ሥ መሠረት ዳኞች የፈረዱበትን ማንኛውንም ሰው ቅጣቱ እስኪወሰን ድረስ ‘ታስሮ’ እንዲቆይ ያዙ ነበር—በጣም ጥቂት ሰብኣዊነት ላይ የተመሠረተ ልዩነት ቢኖርም::

ለዚህ እንደ ምክንያት ይጠቀስ የነበረው የዋስትና መብት ንጹሕ ሆኖ ከመገመት መርኅ ጋር ብቻ የተቆራኘ ስለሆነ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሲባል መብቱም ዐብሮ ቀሪ ይሆናል፣ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ በዋስትና ቢወጣ ሊጣልበት የሚችለውን ቅጣት ፈርቶ ላይቀርብ ስለሚችል የሚጣለው ቅጣት አፈጻጸም ችግር እንዳይገጥመው የሚል ግምት በመያዝ ነበር::

ይሁንና ሁለቱም ምክንያቶች የተሳሳቱ እና የሕግ ፍልስና መሠረት የሌላቸው ስለሆኑ በሥሡ ለማረም ተሞክሯል::

*ለምሳሌ በፌስታል ዐዋጅ ቁ. 1383/2017 አንቀጽ 25(1/ሀ) ሥር ፌስታል በመጠቀም ወይም ለመጠቀም ይዞ በመገኘት ወንጀል ተከሶ የጥፋተኛነት ፍርድ የተሰጠበት ተከሳሽ የቅጣት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በማረፊያ/በማቆያ ቤት እንዲቆይ አዲሱ ሕግ አይፈቅድም

ተባረኩ!
Hailu Hasena (Legal Advocate)


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: