“ተረጂነትን በክህሎት መቀየር ዓላማችን ነው” ወ/ሮ ሀናን ሙሀመድ

- Advertisement -
Sidebar AD

👉ባቡል ኸይር 80 ሰልጣኞችን አስመረቀ፤

​ባቡል ኸይር (የመልካምነት በር) የበጎ አድራጎት ድርጅት “ተረጂነትን በክህሎት የመቀየር” ራዕዩ አካል የሆነውን የሰባተኛ ዙር ሰልጣኞች የምረቃ ፕሮግራም ዛሬ በደመቀ ሁኔታ አከናውኗል።

በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው ለዛሬው ምርቃት የበቁ 80 ወጣቶች፣ በርካታ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ስነ-ስርዓት ተመርቀዋል።

​የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀናን ሙሀመድ በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ በመገኘት ለተመራቂዎቹ የ”እንኳን ደስ አላችሁ” መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወይዘሮ ሀናን በመልዕክታቸው፤ ድርጅቱ ከስድስት ዓመታት በፊት በ16 ሴቶች አነሳሽነት በምግብ ድጋፍ የጀመረው ጉዞ፣ ዛሬ ዜጎችን በሙያ አብቅቶ ወደ አምራችነት ወደሚያሸጋግርበት ምዕራፍ መድረሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል። ሰልጣኞቹም የቀሰሙትን እውቀት ተጠቅመው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲረዱ አሳስበዋል።

​በዛሬው ዕለት ከተመረቁት 80 ሰልጣኞች መካከል 52ቱ በልብስ ስፌት፣ 21ዱ በመሰረታዊ የኮምፒውተር ስልጠና እንዲሁም 7ቱ በቋንቋ ትምህርት የሰለጠኑ ናቸው። ለተመራቂዎቹም እንደየውጤታቸው ማበረታቻ እንዲሆን የልብስ ስፌት ማሽኖችና የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ ይህም ወደ ስራው ዓለም በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተጠቁሟል።

​ባቡል ኸይር እስካሁን ድረስ በሰባት ዙሮች ከ500 በላይ ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን፣ በቀጣይም የራሱን የጋርመንት ፋብሪካ በመክፈት እነዚህኑ ሰልጣኞች በቋሚነት ቀጥሮ ምርቶቹን ለገበያ ለማቅረብ ሰፊ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

​በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ህሊና ሀይሌ እና ከአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ የመጡት ሶሲ ፈርዴሳ፤ ባቡል ኸይር በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግረኞችን በዘላቂነት ለመደገፍና ወደ ስራ ለማስገባት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: