#Ethiopia | በታዋቂው የስፖርት ባለሙያ ፍቃዱ ማሙዬ(ባቢ) መታሰቢያነት የተዘጋጀውና ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው የባቤ ካፕ እግር ኳስ ውድድር፣ በጤና ቡድኖች እና በታዳጊዎች መካከል የተደረጉ ፍልሚያዎችን በማስተናገድ በደመቀ ሁኔታ ተጠናቋል።
በስድስት ኪሎ በሚገኘው ኤፍ ቢ ሜዳ በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ፣ በጤና ቡድኖች ዘርፍ ደጃች ውቤ ሰፈር እንዲሁም በታዳጊዎች ዘርፍ ተስፋ ኮከብ ፍሬ ተጋጣሚዎቻቸውን 2 ለ 1 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ የሻምፒዮናነቱን ክብር ተቀዳጅተዋል።
የውድድሩ ሰብሳቢና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ሳህሉ እንደገለጹት፣ ይህ ውድድር ከ30 ዓመታት በፊት በጉቶ ሜዳ ይካሄድ የነበረውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና በቅርቡ ለተመሰረተው የባቤ ካፕ ተቋም መነሻ የሆነውን የፍቃዱ ማሙዬን ስም ለመዘከር የታለመ ነው። ውድድሩ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ የቀድሞ ተጫዋቾች ጤናቸውን እንዲጠብቁ ከማገዝ ባለፈ፣ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች የክለብ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ብቻ 14 ተጫዋቾች በተለያዩ ክለቦች የታቀፉ ሲሆን፣ ዘንድሮም ውድድሩ ሳይጠናቀቅ አንድ ተጫዋች ለክለብ መመረጡ የቶርናመንቱን ስኬታማነት ማሳያ ሆኗል።
በዘንድሮው ውድድር ላይ በራሳቸው የፋይናንስ አቅም የሚንቀሳቀሱ 12 የጤና ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን፣ አምስት የፕሮጀክት ታዳጊ ቡድኖች ደግሞ በነጻ እንዲወዳደሩ ተደርጓል።
በታዳጊዎች የፍጻሜ ጨዋታ ተስፋ ኮከብ ፍሬ ዘበኛ ሰፈርን አሸንፎ ዋንጫውን ሲያነሳ፣ በጤና ቡድኖች ደግሞ ደጃች ውቤ ሰፈር በጉቶ ሜዳ ላይ በነበረው ጨዋታ አሸናፊ ሆኗል።
በተጨማሪም በውድድሩ ላይ በታየው መልካም ስነ-ምግባር የገዳም ሰፈር ቡድን የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
የአራዳ እና የጉለሌ ክፍለ ከተማ ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዚህ መርሃ ግብር ላይ፣ አዘጋጆቹ ውድድሩን ለማሳካት የአዲስ አበባ ወጣትና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም የጉለሌ ክፍለ ከተማው አስተዳደር ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የባቤ ካፕ አዘጋጆች በቀጣይ ዓመት የታዳጊ ቡድኖችን ቁጥር ወደ 16 በማሳደግ፣ ወጣቶች በስፖርቱ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከርና የተሻሉ ዜጎችን ለማፍራት እቅድ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱም አስታውቀዋል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen








No comments yet.