የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ለሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እውቅና ሰጠ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ዛሬ በካፒታል ሆቴል ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በሆቴል ዘርፉ ላሳየው የላቀ የሥራ አፈጻጸምና አስተዋጽኦ የክብር እውቅና ሰጠ።

ማህበሩ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከማካሄድ ባለፈ በሆቴሎች ወቅታዊ ሁኔታና ኢትዮጵያ በቅርቡ በምታስተናግደው የኮፕ 32 (COP 32) ዓለም አቀፍ ጉባኤ ስትራቴጂካዊ ዝግጅቶች ላይ ያተኮረ ሰፊ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

​በዚሁ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የማህበሩ አባላት በተገኙበት ጉባኤ ላይ በርካታ ዓመታዊ አጀንዳዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ከተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የማህበሩ ዓመታዊና የኦዲት ሪፖርቶች ቀርበው የጸደቁ ሲሆን፣ የአባልነት ክፍያና የአከፋፈል ሥርዓትን ማሻሻል እንዲሁም የሆቴል ቢዝነስን ይበልጥ ለማሳደግ ከባለሀብቶችና ከባለሙያዎች የሚጠበቁ ስራዎችን በተመለከተ በጥልቀት ተመክሮበታል።

​የፓናል ውይይቱ ዋነኛ ትኩረት በነበረው የኮፕ 32 ጉባኤ ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው ለዚህ ትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ማህበሩ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ተገልጿል። ከተለያዩ ሀገራት ለሚመጡ በርካታ እንግዶች የሚመጥንና ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ማህበሩ ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ በስፋት ተብራርቷል።

​የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ባለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ የአባላቱን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ እንዲሁም ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር የሀገሪቱን የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ እድገት በጽኑ ሲደግፍ የቆየ ተቋም ነው።

በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ከ180 በላይ አባል ሆቴሎችን በውስጡ አቅፎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ማህበር መሆኑ ይታወቃል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2