በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ድንቅ ሥራ የሰሩ፣ ተአምረኛና ገዳማዊ አባት ናቸው። እኒህ ታላቅ ጻድቅ ሐዋርያዊ አባት አቡነ ዓምደ ሥላሴ የካቲት 27 ጎጃም ውስጥ ነው የተወለዱት።
የካቲት 17 ቀን መንኩሰው ወደ ተጋድሎ ገብተዋል። በተለያዩ ገዳማት በነበራቸው ቆይታም እመቤታችን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን በነበራቸው ፍቅር ይታወቃሉ። ጻድቁ በበርካታ ገዳማት የነበሩ ሲሆን በገዳማዊ ሕይወታቸው በትህርምት፣ በጸሎታቸውና በተጋድሏቸው ዛሬም ድረስ ከሚታወቁ አባቶች አንዱ ናቸው። ጻድቁ አባታችን ዓምደ ሥላሴ ከሚነገሩላቸው ታሪኮች ቅድሚያውን የሚይዘው የተዋሕዶ ጠበቃነታቸው ነው።
በ1603 ዓ.ም ጴጥሮስ ወይም ፔድሮ ፓኤዝ የሚባል ካቶሊካዊ ከሀዲ ወደ ሃገራችን ገብቶ ነበር መኖር ጀመረ፡፡ ከዚያም ውስጥ ለውስጥ ሲሰብክ ቆይቶ በ1609 ዓ.ም ነገሩ በመገለጡ እነ ራስ ዮልዮስ ለሃይማኖታቸው ጠዳ ላይ ተዋግተው ግንቦት 6 ቀን ተሰው። በ1622 ዓ.ም አጼ ሱስኒዮስ ከነቤተሰባቸው ተጠምቀው ካቶሊክ ሆኑ፡፡ ይህ ነገር ሲሰማ ወንድ ሴት፣ ትልቅ ትንሽ ሳይመረጥ በገጠሩም፣ በከተማውም፣ በገዳሙም ያሉት ሁሉ የተዋሕዶ ልጆች መንቀሳቀስ ጀመሩ። በ1626 ዓ.ም ካቶሊክ የኢትዮጵያ እምነት ነው ብለው ሲያውጁ ግጭቱ በይፋ ተጀመረ። “ተዋሕዶን ካልካዳችሁ” በሚል በቀን እስከ ስምንት ሺህ ሰው በሰይፍ ታረደ። ይህን ያደረጉት ደግሞ አልፎንሱ ሜንዴዝ፣ ንጉሡ ሱስንዮስና ጀሌዎቻቸው ነበሩ።
በጊዜውም ከቤተ መንግሥት የሱስንዮስ ሚስት እነ ንግሥት ወልድ ሰዓላ፣ ከጻድቃን አበው ዘርዓ ቡሩክ ዘግሸን፣ ሐራ ድንግል ዘደራ፣ ምዕመነ ድንግል ዘጩጊ፣ ዓምደ ሥላሴ ዘማኅበረ ሥላሴ፣….. ከቅዱሳት እነ ፍቅርተ ክርስቶስ፣ ወለተ ጴጥሮስ፣ ወለተ ጳውሎስ፣ እኅተ ጴጥሮስ፣….. ለሃይማኖታቸው ተዋሕዶ ጥብቅና ቆመው ሕዝቡን አስተማሩ፤ መከራም ተቀበሉ። ብዙ ኢትዮጵያውያን የመከራ ጽዋን ተጐንጭተው በክብር ሰማእትነት ከተቀበሉ በኋላ የእግዚአብሔር ፍርድ ተገለጠ። በጻድቃኑ በእነ አባ ዓምደ ሥላሴ ሐዘን ንጉሡ ታመሙ ከዚያም ምላሳቸው ተጐልጉሎ ወጣ። በዚህ ጊዜ አቤቶ ፋሲለደስ ለአባ ዓምደ ሥላሴና ለሌሎቹ ቅዱሳን “አባቴን አድኑልኝ! ተዋሕዶም ትመለስ።” አላቸው።
ጻድቁም ከባልንጀሮቻቸው ጋር ጸልየው ንጉሡን አዳኗቸው። እርሳቸውም “ፋሲል ይንገሥ! ተዋሕዶ ሃይማኖት ይመለስ! የሮም ሃይማኖት ይፍለስ!” ብለው አሳወጁ። ከዚህ በኋላ አጼ ፋሲል ሲነግሡ አባ ዓምደ ሥላሴ ለገዳማቸው ብዙ ቦታ አስከልለው በተጋድሎ ኑረው የካቲት 27 ዐርፈዋል።
ገዳማውያን ሃይማኖት ሲነካ አንገታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ሕዝቡን ለማጽናናትና ለማስተማር ከገዳማቸው ይወጣሉ እንጂ በተጋድሎ ጸንተው፣ በትህርምት ረግተው፣ በጸሎት ተግተው ከዓለም ርቀው ነው የሚኖሩት፡፡ በዓለም ላለነው ለኛና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ለሀገራችንም ይጸልያሉ፡፡ ገዳማቸውን በመርዳት፣ በዓታቸውን በማጽናት ከበረከታቸው እንሳተፍ፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444
Source: FastMereja









No comments yet.