#Ethiopia | “ቴአትርን በፍቅር እወደዋለሁ። ለቴአትር ሙያ የራሴን በጎ አሻራ ማሳረፍ እፈልጋለሁ!” ብላለች።
አርቲስቷ ‘ጥቁር እንግዳ’ ቴአትርን ፕሮዲዉስ ያደረገችና የተወነች ሲሆን በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆና ለመድረክ እንዳበቃችው ተናግራለች።
“ከባድ ነበር! ብዙ ህመም ስቃይ ነበረው። እንደልምድ ብዙ ተምሬበታለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን ‘ጥቁር እንግዳ’ ለመድረክ በቅቷል። ተቀባይነቱም ደስ ይላል። የበለጠ ጥቂት ነገሮች ተስተካክለው በነጻነት ትወናችንን ከፍ አድርገነው ስንዋሃድ ተመልካች እንደሚደመምበት አልጠራጠርም! በእዚህ አጋጣሚ የጥቁር እንግዳ ቴአትር አባላትን አመሠግናቸዋለሁ።”
ስለቀጣይ ስራዋም እንዲህ ብላለች
“አሁን ማሰብ የምፈልገው ስለቀጣዩ ስራ ነው። አንድ ሁለት ወጥ ስራ እጄ ላይ አለ። አንዱ ካናዳ አገር የሚገኘው የልዑል ዳዊት “ጋሜ” የተሰኘ ተውኔት ነው። ሁለተኛው የደራሲ ውድነህ ክፍሌ “የህልሜ ጓደኛ” የተሰኘ በሁለት ሰው ብቻ የሚሰራ ኮሜዲ ስራ ነው። በእዚህ አጋጣሚ ውድዬን ማመስገን እፈልጋለሁ። በዘመኔ እንደእሱ ያለ ደግና ቅን ሰው አይቼ አላውቅም። በእዚህ አጋጣሚ አመሠግንሃለሁ።
“አስጀምሮ የሚያስጨርሰው እግዚአብሔር ይርዳኝ እንጂ እንደኔ ሀሳብ በቅርቡ ሁለቱን ስራዎች በጣም የማከብረው፣መምህሬ አዘጋጅ ተስፋዬ ገ/ማርያም እና አንደኛውን ደግሞ ሳሙኤል ተስፋዬ እንዲያዘጋጁት እፈልጋለሁ።” ብላለች።
ማርታ ግርማ በርካታ ፊልምና ተከታታይ ድራማ ላይ ተውናለች።
ለአብነትም ባለቀለም ህልሞች፣ ያረፈደ አራዳ፣ ትንታግ፣ ሰርግ በአሜሪካ፣ በራድ ፍም፣ ሰው እኮ፣ አስማማው፣ ረመጥ እና ሰርፕራይዝ የተሰኙ ፊልሞችን መጥቀስ ይቻላል።
በተከታታይ ድራማም ውርስ፣ አየር ላይ፣የተገፉት፣ የሌሊት ጧፍ እና በህግ አምላክን ማንሳት ይቻላል። እንደቴአትር ምሩቅነቷ ቴአትር ላይ ብዙም ባትሰራም “ህንደኬ” ፣ “ህልም እልም” በተሰኙ እና በጋሽ ተስፋዬ አበበ(ፋዘር) የቴአትር ማደራጃ ቴአትሮችን ሰርታለች። በአምባሳደርነትም ለተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅት አገልግሎትን እየሰጠች ነው።
አሁን ደግሞ በዓለም ሲኒማ “ጥቁር እንግዳ” ቴአትርን በ12 ሰዓት ፕሮዲዉስ አድርጋ እያሳየች ነው።


Source: GetuTemesgen









No comments yet.