በሲዳማ ባህል በሽማግሌዎች ጉዳይ ላይ ሀሳብ ከመስጠት በፊት ሽማግሌዎች ሺህ ጊዜ ቢያጠፉ እንኳን ለግርማቸው አክብሮት መስጠት ያለነውና በቅድሚያ Gu gaarinsara! (ከቀደምት አባቶቻቸው ለተሰጣቸው ሞገስ እግዞኦ) ብዬ አክብሮቴን እገልፃለሁ።
ቀጥዬ “ሽማግለዎች አወገዙ!” በሚለው የሰሞኑ አጀንዳ ላይ ሀሳቤን እንደሚከተለው አቀርባለሁ። በእውነቱ በሲዳማ ባህል አንድ ጭሜሳ (ሽማግሌ) ከአንዱ ወገን አቤቱታ የሰሙ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የሌላኛውን ወገን አቋም “Hanni xa’me afeemmona!” [እስቲ ጠይቄ አረጋግጣለሁ] ይላሉ። የሲዳማ ጭሜሳ ከአንድ ወገን ብቻ ሰምቶ የሚያወግዝ ባህል የለውም። የግራ ቀኙን ሰምቶ፣ እውነታውን በሸንጎው አብጠርጥሮ አውጥቶ ነው በጋራ ከውሳኔ የሚደርሰው።
በሌላ በኩል የነፍስ ግዲያም ቢሆን የሲዳማ ጭሜሳ ያስታርቃል እንጂ ውግዘትን እንደ መፍትሄ ወስዶ አያውቅም። የሲዳማ ጭሜሳ ውበቱ በአፊኒ ባህሉ ፈልጎ ግልፅ ማድረጉ ላይ ነው የአጀንዳውን መነሻና እውነቱን። በሁለት ወገኖች መካከል የፈለገ ጥልና ቅራኔ ቢኖር እንኳን “Amo amme seemma’ya giddora e’e (ኑ ወደ ቡሉኮዬ ውስጥ ግቡ) እያለ ያሰባሰባል እንጂ ነገ የሚያድጉ ልጆችን አይበትንም። ከጥንት ጀምሮ የምናውቀው ባህል ይሄ ነው። የቱ ጋ መጥቶ እንደተቀላቀለብን አላውቅም። ጊዜና ማጋኖ ግን የሚሳነው ነገር የለውምና ወደ ቀደመው ሃቀኛ ወግና ሥርአታችን ይመልሰናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የኔ አላማ ባህሉን ሳይበረዝ ሳይከለስ ማሳወቅ ነው። ይሄው ነው!!
Via: ሳሙኤል በላይነህ
Source: FastMereja









No comments yet.