#ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ…

- Advertisement -
Sidebar AD

የስሙ ትርጓሜ “ጽኑ በኩር” ማለት ነው፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም ሲሆን በመጀመሪያ የተጠራ ሐዋርያ ነው፡፡ በመጀመሪያ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረ ቢሆንም መጥምቁ የጌታችንን መንገድ ሲጠርግና ስለ ክርስቶስም ሲሰብክ ስለሰማው በዚያው የጌታችን ደቀ መዝሙር ሆኗል፡፡ ከሰው ጋር ፈጥኖ የመግባባት ችሎታ ስለነበረው በሐዋርያትም ዘንድ እንደ አስተባባሪ ይቆጠር ነበር፡፡ ጌታችን 5 እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አበርክቶ ሕዝቡን ሲመግብ እንጀራውንና ዓሣዎቹን የያዘውን ወጣት ወደ ጌታችን ወስዶ እንዲባረክ ያደረገው እንድርያስ ነው፡፡ በዚህም የወጣቶች ሐዋርያ ይባላል፤ ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ፡፡ ሐዋርያው በሩሲያ፣ በቢታንያ፣ በገላቲያና በሩማንያ ወንጌልን ሰብኮ ብዙ ክርስቲያኖችን አፍርቷል፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳን ተክቶ ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር ከተቆጠረ በኋላ ሰውን የሚበሉ ሰዎች ወዳሉባት “እስኩቴስ” ወደተባለች የሩሲያ ክፍል ሄዶ ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ዕጣ ደረሰው፡፡ ቅዱስ ማትያስም አገራቸው እንደደረሰ ዐይኑን አውልቀው አሠሩት፡፡ ምግባቸውም የእንግዳ ሰው ሥጋ ነው፡፡ በልማዳቸው መሠረት ገና እንደያዙት ዐይኖቹን ዐውልቀው እሥር ቤት ይጥሉታል፡፡ እስከ 30 ቀን ድረስም ሳር እያበሉ ያስቀምጡትና በ30ኛው ቀን ከእሥር ቤታቸው አውጥተው አርደው ይበሉታል፡፡ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ ወንጌልን እየሰበከ በግሪክ አገር ሳለ ክብር ይጋበውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና “ሰውን የሚበሉ ሰዎች ማትያስን ይዘው አሥረውታል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ ሊበሉት ከእሥር ቤታቸው ያወጡታልና አንተ አሁን ወደ እነዚያ ሰውን ወደሚበሉት ሰዎች አገር ሂድ” አለው፡፡

እንድርያስም “ጌታዬ ፈጣሪዬ የቀረው ሦስት ቀን ከሆነ እንዴት እደርሳለሁ? ባይሆን ፈጥኖ የሚያወጣው መልአክ ላክለት” አለው፡፡ ጌታችንም “እኔ ሀገሪቱን ነይ ካልኳት በውስጧ ከሚኖሩት ሁሉ ጋር ትመጣለች፤ ፈቃዴ ግን አንተና ደቀ መዝሙሮችህ እንድትሄዱ ነውና ነገ በጠዋት ተነሥታችሁ ወደ ባሕሩ ሂዱ፣ የተዘጋጀች መርከብም ታገኛላችሁ” ብሎት በክብር ዐረገ፡፡ በነጋው ወደ ወደቡ ሲደርሱ ጥሩ የተዘጋጀች መርከብንም አገኙ፡፡ ጌታችንም በሊቀ ሐመር አምሳል ተገለጠለት ነገር ግን እንድርያስ አላወቀውም ነበር፡፡ በመርከቡ ሲጓዙም እንቅልፍ ጣላቸውና መላእክት ወስደው በባሕሩ ዳርቻ አስቀመጧቸው፤ መርከቡ ግን አልነበረም፡፡ እንድርያስም የመርከቡ ቀዛፊ ጌታችን መሆኑን አሁን ዐወቆ ሲጸልይ ጌታችን ተገለጠለትና ማትያስንና አብረውት ያሉትን ከወህኒ ሳይፈራ እንዲያወጣቸው ነገረው፡፡

ቅዱስ እንድርያስና ደቀ መዛሙርቱም መትያስንና እስረኞቹን ሁሉ ነጻ አወጧቸው፡፡ ሰው የሚበሉትን የከተማዋ ሕዝቦችም በድንቅ ተአምራት መልሰው ወንጌል ሰብከው አጠመቋቸው፡፡ ቅዱስ እንድርያስ የቍስጥንጥንያ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስም ነው፡፡ በግሪክ ሲያስተምር ከሃዲያን ይዘው በ60 ዓ.ም ታኅሣሥ 4 ቀን ሰቅለው ገድለውታል፡፡ ሊሰቅሉት ሲወስዱትም “ጌታዬ በተሰቀለበት ዓይነት መስቀል አትስቀሉኝ” በማለት ሲለምናቸው እነርሱም ፍቃዱን ፈጽመውለት የእንግሊዝኛው ኤክስ (X) ፊደል ቅርጽ ባለው መስቀል ላይ ሰቅለውታል፡፡ ስኮትላንዶች የቀኝ የእጆቹን ጣቶች በአንድ መነኩሴ አማካኝነት ስላገኙ ሐዋርያው እንድርያስን ‹‹ጠባቂያችን›› ነው እያሉ ይመኩበታል፡፡ በረከቱ ትደርብ አሜን፡፡

በገዳማዊ ኑሮ ያሉትን እየረዳንና በዓታቸውን እያጸናን የበረከታቸው ተሳታፊ እንሁን፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444



Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1