የድምጻዊ አንዱአለም ጠበቃ “ቀነኒ በርካታ ጊዜ ራሷን ለማጥፋት መሞከሯን ከማስታወሻዋ ላይ ተገንዝቤያለው” ሲል ተከራከረ

- Advertisement -
Sidebar AD

የድምጻዊ አንዱአለም ጠበቃ “ቀነኒ በርካታ ጊዜ ራሷን ለማጥፋት መሞከሯን ከማስታወሻዋ ላይ ተገንዝቤያለው” ሲል በችሎቱ ተከራከረ። በፍቅር አጋሩ ግድያ ቀነኒ አዱኛ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኘው የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊ አንዱአለም ጎሳ ዛሬ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ/ም ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበ።

ተጠርጣሪው አንዱአለም ጎሳ ዛሬ ጠዋት አራዳ በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት ከጠበቃው ጋር በቀረበበት ወቅት ፖሊስ በተሰጠው 12 የምርመራ ቀናት ውስጥ ያሰባሰበውን ማስረጃ ለችሎቱ አቅርቧል።

ዛሬ በዋለው ችሎት ፖሊስ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ/ም በተሰጠው 12 ተጫማሪ የምርመራ ቀናት ውስጥ በሞዴል ቀነኒ አዱኛ ሞት ላይ 15 ተጨማሪ የሰዎች በአጠቃላይ የ28 ሰዎች ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ገልጿል።

እንዲሁም በቀነኒ መኖሪያ ቤት ውስጥ በሚገኝ ምንጣፍ ላይ የተደረገው ምርመራን ጨምሮ የተለያዩ ናሙናዎችን በመውሰድ ለፎረንሲክ ምርመራ ለፌዴራል ፖሊስ መላኩን እና የምርመራው ውጤት ግን እስካዛሬ አለመድረሱን ገልጿል።
በተጨማሪም በሟቿ እና በተጠርጣሪው የእጅ ስልክ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ወደ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተልኮ የምርመራው ውጤት እየተጠበቀ እንደሚገኝ ለችሎቱ አስረድቷል።

ሳይበሰበሰቡ የቀሩ ማስረጃዎች ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት ላይ ከቀረቡት የምርመራ ውጤቶች ጋር እንደ ተጨማሪ ግብዓት እንዲካተትለት የጠየቀው ፖሊስ መሰብሰብ ያለባቸውን ተጨማሪ ማስረጃዎች ለማሰባሰብ ተጨማሪ የምርመራ ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።
መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ፖሊስ በአስክሬን መርመራ ቀነኒ “ከፍ ካለ ቦታ ላይ ወድቃ ህይወቷ ማለፉን” ጠቁሟል። “ነገር ግን የአስከሬን ምርመራ ውጤትን በተመለከተ ከህክምና ባለሙያዎች ተጨማሪ ማብራሪያ በመጠየቁ ውጤት እስኪደርሰው ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው መጠየቁ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ፖሊስ በዛሬው ችሎት እንደገለጸው ማስረጃውን ከያዙት የህክምና ባለሙያዎች መካከል የተወሰኑት በአገር ውስጥ እንደሌሉና እነሱን ለማግኘት የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ መሆኑን በመግለጽ ውጤቱን እስኪቀበል 14 ተጨማሪ ምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል። የአንዱአለም ጎሳ ጠበቃ ሊበን አብዲ በበኩሉ፤ ፖሊስ ተመሳሳይ ምክንያት በማናቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ “ተቀባይነት የሌለው” በመሆኑ ተጠርጣሪው የዋስትና መብት ሊጠበቅለት ይገባል ሲል ተከራክሯል።

የተጠርጣሪው ጠበቃ የቀነኒ አዱኛ የማስታወሻ ደብተር በእጁ ላይ እንዳለ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። በማስታወሻ ደብተሩ ላይ [ቀነኒ] ብዙ ጊዜ እራሱን ለማጥፋት ከመጠን በላይ መድሃኒት መውሰዷን መረዳቱን ለችሎቱ ተናግሯል።

የመቷ ምክንያትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ሲል ተከራክሯል። አክሎም አንዱአለም ጎሳ በቀነኒ ሞት ውስጥ መሳተፉን የሚያረጋግጥ የሰው ማስረጃ እና የምርመራ ሰነድ መረጃ እንደሌለ በመግለጽ፤ ይህም “ንፁህ መሆኑን የሚያረጋግጥ በመሆኑ” ተጠርጣሪው የዋስ መብቱ ተጠርብቆለት ወደ ቤት ሄዶ ፍቅረኛውን ህልፈተ ሃዘነ እንዲያወጣ ጠይቋል።

ከዚህም በተጨማሪ ‘ኢትዮ ፎረም’ የተሰኘ ዩቲዩብ ሚዲያ ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች በባለፈው ችሎት ተጠርጣሪው አንዱአለም ጎሳ ለመጪው የትንሳኤ በዓል ኮንሰርት ስላለው የዋስትና ጥያቄ እንዳቀረበ አድርገው መዘገባቸው ”በቀነኒ ቤተሰብ እና የሚወደው ማሀበረሰበ እንዲጨክንበት ታስቦ የተደረገ የስም የማጥፋት ዘመቻ ነው” ሲል ገልጾ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እንዲመለከተው ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ ፖሊስ ያቀረበውን የምርመራ ውጤት እና በሁለቱም ወገኖች የተነሱትን ጥያቄዎች መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ መጋቢት 30 ቀን ከጠዋቱ 3፡00 ቀጠሮ ሰጥቷል። ሞዴል እና የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነችው ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ ከእጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ውዳሴ ከተሰኘው ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በመውደቋ ህይወቷ ማለፉ ይታወቃል።



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: