“ መመሪያው፣ የቤት ሰራተኞች መሰረታዊ መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው እንዲሰሩና፣ ጉልበታቸው ሲደክምም እንደ ጡረታ ያሉ የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል ” – የቤት ሰራተኞች ማህበር ህብረት
#Ethiopia | የቤት ሰራተኞችን የጡረታና የሌሎችም ማህበራዊ ዋስትና አገልግሎቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ የስራ ቅጥር ውልና መመሪያ በቅርቡ እንደሚወጣ፣ አንድነት የኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች ማህበር ህብረት አስታወቀ፡፡
የህብረቱ ፕረዝደንት ሒሩት አበራ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃለመጠይቅ፣ መመሪያው በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግብአት የታከለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መመሪያው ፀድቆ በስራ ላይ ሲውል፣ የቤት ሰራተኞችን መሰረታዊ መብቶች የሚያስጠብቅ፣ ከአሰሪዎቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚያስተካክልና የስራ ከባቢያቸውንም ምቹ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን፣ መመሪያውና የስራ ቅጥር ውሉ፣ የቤት ሰራተኞች ጉልበታቸው ሲደክም እንደ ጡረታ ያሉ የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡
ፕረዝዳንቷ ሒሩት አበራ በዚህ ጉዳይ ላይ በዝርዝር ምን አሉ ?
“ የስራ ቅጥር ውሉንና መመሪያውን እያዘጋጀው ያለው የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ነው፡፡ መመሪያው በቅርቡ ይወጣል፡፡ በጣም በቅርብ፡፡
መመሪያው ለሰራተኛውም ለአሰሪውም የሚጠቅምና ግንኙነታቸውንም የሚያሻሽል ነው የሚሆነው፡፡
የስራ ቅጥር ውሉና መመሪያ በአሁኑ ወቅት ያለውን የሀገሪቱን ነባራዊ ኹኔታ ከግምት ያስገባ ነው፡፡
መመሪያው የቤት ሰራተኞችም አሰሪዎችም መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ፣ የቤት ሰራተኞች የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ተጠቃሚዎች አይደሉም፡፡ በዚህ መመሪያ መሰረት ግን የቤት ሰራተኞች እንደማንኛውም ሰራተኛ መብቶቻቸው ይከበራሉ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መሟላት ያሉባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡
እነዚህ ዜጎች እንደማንኛውም ሰራተኛ መታየት አለባቸው ካልን፣ እነሱም ሊያሟሉዋቸው የሚገቡ መስፈርቶች ይኖራሉ፡፡ ሰራተኞቹ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ያገኙ መሆን አለባቸው፡፡
የቤት ሰራተኞች ለገበያው ብቁ እንዲሆኑም ስልጠናዎች ይሰጣሉ፣ ያሉባቸውን የሙያ ክፍተቶች ለመሙላት ይሰራል፡፡ አሰሪውም ለሚከፍለው ደመወዝ ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ በሀገር ደረጃ፣ ህገወጥ ስደትን ለመቀነስ የሚያስችል ይሆናል ብለን ነው የምናምነው፡፡
ነገሮችን ሰፋ አድርጎ የሚያይ መመሪያ ነው እየወጣ ያለው፡፡
መመሪያው ከወጣ በኋላ፣ በአፈፃፀም ወቅት ተግዳት እንዳይገጥመው፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወንን እንገኛለን፡፡
በአሁን ወቅት የቤት ሰራተኞች በስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚዋዋሉት ውል ምንም ዓይነት ህጋዊ መሰረት የሌለው፣ ሐላፊነትን የማይሰጥና መብትና ግዴታን የማይለይ ነው፡፡
መብትና ግዴታውን የማያውቅ ሰው ደግሞ የሚጣልበት ቅጣት አይኖርም፡፡ ይህ መመሪያ ግን በቤት ሰራተኞች አስተዳደር በኩል ያሉትን ችግሮች ይፈታል፡፡
ለአሰሪና ሰራተኛ መብትንና ግዴታን ለይቶ የሚሰጥ ነው፡፡ ለሁለቱም ጠቃሚ የሆነ፣ የቤት ሰራተኝት ዘርፍ፣ ሞያተኞችም መርጠው የሚገቡበት የስራ መደብ እንዲሆን የሚያደርግ መመሪያ ነው፡፡
በቤት ሰራተኝነት ዘርፍ፣ ለአስር አመታት ያህል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደረጉና ጥናትም ያደረጉ አንድ ባለሙያ በበኩላቸው፣ ዘርፉ ህጋዊ መሰረት ቢኖረውና በህጋዊ ማዕቀፍ ቢደገፍ፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቃሚ የሆነ ኢንዱስትሪ መሆን ይችላል ” ብለዋል፡፡
ከአራት አመታት በፊት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መሰረት፣ በሀገሪቱ ወደ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰራተኞች እንዳሉ የገለፁት ባለሙያው አቶ መሲ ቸኮል ማሬ፣ እነዚህ ዜጎች የተለያዩ ችግሮች እንደሚደርሱባቸውም በጥናት አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ባለሙያው አቶ መሲ ቸኮል ማሬ ምን አሉ ?
“ በጥናታችን መሰረት፣ ከ8 አመት ህፃናት ጀምሮ በቤት ሰራተኝነት የሚያገለግሉ ሴቶች አሉ፡፡ በተለይም ህጻናቱ፣ ከገጠር ወደ ከተማ እየወሰዱ በቤት ሰራተኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠናል፡፡
ከገጠር ወደ ከተማ ወደሚገኝ አሰሪ ሲላኩ፣ ትምህርት ይማራሉ በሚሉ ምክንያት ነው፡፡ በጥናታችን እንዳየነው ግን ብዙዎቹ አልተማሩም፣ ወይም ያቋረጡ ናቸው፡፡
አሰሪዎች ደሞዛቸውን እየቆረጡ ለቤተሰቦቻቸው እንደሚልኩ፣ ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው፣ በዚህም ላልተፈለገ እርግዝና ተዳርገው እንደሚወልዱ አይተናል፡፡
ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ፣ እንዲሁም የጤና ችግር ይደርስባቸዋል፡፡ ወደ እምነት ስፍራዎች እንዲሔዱና እንዲያመልኩ አይፈቀድላቸውም፣ በቂ ምግብና፣ እረፍትና እንቅልፍ አያገኙም፣ ምቹ የመኝታ ቦታም አይሰጣቸውም፡፡
በአሰሪዎቻቸው የአስገድዶ መድፈር ችግር ይደርስባቸዋል፣ በዚህም ወልደው ጎዳና የሚወጡበት ሁኔታ አለ፡፡
ጡረታና የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ባለመኖሩ አብዛኞቹ መጨረሻቸው ጎዳና ይሆናል፡፡
‘ እቃ ሰርቃችኋል፣ ሰብራችኋል፣ ጥፋት ፈፅማችኋል ‘ ተብለው በአሰሪዎቻቸው ያለደመወዝ ይባረራሉ፡፡
በቤት ሰራተኝነት ሲቀጠሩም ያለ የስራ ውል ስለሆነ፣ ደመወዛቸውን ሲከለከሉ፣ ጥቃትም ሲደርስባቸው ከፍትሐብሔርና ከወንጀል ህጉ ውጪ ሌላ ህግ ስለሌለ፣ ፍትሕ አያገኙም፡፡
ወደ ሴቶች ጉዳይ መስሪያ ቤቶች ሲሔዱም፣ ‘ የእናንተ ጉዳይ እኛን አይመለከተንም ‘ ይባላሉ፡፡
መገለል፣ አድልዎ፣ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማንቋሸሽ ይደርስባቸዋል፡፡
የቤት ሰራተኛ ነኝ ብለው ደፍረው እንዳይናገሩ አድርጓቸዋል ችግሩ፡፡
አሰሪዎች ደግሞ ከሙያ አንፃር፣ ከመታመን አኳያ፣ የቤት ሰራተኞች ክፍተት እንዳለባቸው ያነሳሉ፡፡ ይህ ዘርፍ በህግ ቢደገፍ አሰሪዎችም ሰራተኛውም ግዴታቸውንና መብታቸውን ያስከብራሉ፡፡
ዘርፉ በህግ ከተደገፈ ዜጎች ሀገር ለቀው የህገወጥ ስደት ሰለባ አይሆኑም፡፡ ዘርፉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚታይበትና ብዙ የሰው ሀይል የሚይዝ በመሆኑ፣ ዜጎች እንደ አንድ የስራ ምድብ ሊያዩት ይችላሉ፡፡
ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን የሚደግፉበትም ይሆናል፡፡ ዘርፉንም ለማሳደግ ያስችላል፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋፅኦ እንዲኖረውም ያደርጋል ” ብለዋል።
#tikvah
ባሉበት ሆነው ትኩስ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኝት ከስር ያሉትን ሊንኮች ይጫኑ ቤተሰብ ይሁኑ።
“””””””””””***””””””””””
ዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/@getutemesgenet
ፌስቡክ ገጽ: https://web.facebook.com/getu26
ቴሌግራም ገጽ: https://t.me/getutemesgenet
ቲክቶክ ገጽ: https://www.tiktok.com/@getutemesgenet
ኢንስታግራም ገጽ: https://www.instagram.com/getutemesgenet
ኤክስ: https://x.com/getutemesgenet
ኢንግሊዘኛ ድረ-ገጽ: https://getutemesgen.et
አማርኛ ድረ-ገጽ: https://amharic.getutemesgen.et
Source: GetuTemesgen









No comments yet.