❗️
ከሰሞኑን የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም Ethiopian society partnership በተባለ ድርጅት የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል
‹የመሠረተ ትምህርት ዘመቻን ተግባራዊ ለማድረግ ላበረከቱት አስተዋፅዖ› በሚል ለሽልማት ያበቃቸውና
5 ሚሊየን 537 ሺህ ባለሃገር ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደረገው እድገት በህብረት
ለፍቅር፣ ለብልጽግና፣ ለጸጋና ለእድገት ቀናኢ የሆነ ትውልድ በአገራችን ተነሳ። ያባቶቹን የአድዋ፣ ዶጋሌ ፣የማይጮ የሽሬ፣የመቅደላ፣ የጉንደት፣የመተማ፣ የኤሊባቡር፣ የጎሬ፣ የብቸና፣ የመላ ጎጃም፣ የሜጫ፣ የሸዋና የመላ ጎንደር አርበኝነትን ገድል ካባቶቹ ሲሰማ ያደገው ትውልድ፤ በመንፈስም በስጋም ከነሱ የወሰደውን የጀግንነት ታሪክ በእድገት ለመለወጥ የዛሬ ሀምሳ አምስት ከአጥናፍ እስከአጥናፍ “ኢትዮጵያ ትቅደም “የሚል መፈክር ይዞ ተነሳ ። የእድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ።
የደርግ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የህብረተሰብዓዊነት ርዕዮትን ማወጁን ተከትሎ ቀዳሚ ተግባሩ ካደረጋቸው ርምጃዎች “የእድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ” አንዱ ነው፡፡
እኛም ሃምሳ አመታትን ወደኋላ ተጉዘን ይህን ከኩባ የትምህርት ዘመቻ ቀጥሎ ባመጣው ለዉጥ የሚነሳውን የትላንት ታሪክ ሰሚ ጆሮ ያለው ከተገኘም የነገ የተሻለች ሃገር ለመፍጠር መንደርደሪያ መሰላል ይሆናል ብለን በማመን እነሆ በዚህ መልክ አቅርበነዋል ።
ታሪኩ የሚጀምረዉ በነሐሴ 28 ቀን 1966 ዓ.ም ነዉ ። ደርግ ዘውዳዊውን ስርዓት ገርስሶ መንበረ ስልጣኑን ከመቆናጠጡ ጥቂት ቀናት በፊት ነበር የዘመቻው ሃሳብ የተፀነሰው ።
ጥናቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ጥቅምት 16 ቀን 1967 ዓ.ም የዕድገት በሕብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ጠቅላይ መምሪያ ተቋቁሞ ሥራውን ጀመረ። ሻምበል ኪሮስ አለማየሁም ዘመቻውን እንዲመሩ በሊቀመንበርነት ተመደቡ።
በዚህ መልክ እስከ ታህሳስ ታህሳስ 12 ቀን 1967 ዓ/ም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጂት ሲደረግ ቆይቶ የዩኒቨርስቲ፣ የኮሌጅ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራን ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘምተው ገብሬውን የማንቃትና የማደራጀት ሥራ ይሰሩ ዘንድ ታህሳስ 12 ቀን 1967 ዓ/ም የእድገት በኅብረት የሥራ ዘመቻ በብሔራዊ ደረጃ በይፋ ታወጀ ፡፡
ለዚህ ዘመቻ ቅስቀሳ በርካታ ድምጻዊያን ዘፈን አወጡ፡፡
የጥላሁን ገሠሠ “ለዕድገት በህብረት እንዝመት”፣
የጥላዬ ጨዋቃ
“አሸወይና ማለቴ ለዘማቿ እህቴ”፣
የታምራት ሞላ “በህይወት ግቡ በህይወት
ዘመቻ ምትሄዱ ለዕድገት በህብረት”፣
እንዲሁም “ሀገሬ ኢትዮጲያ የሻይ ቤት የኬክ ቤት ሆነሽ እንዳትቀሪ፣ አስበውልሻል ትልቅ ኢንደስትሪ፣
ለእድገት ተሰልፏል ተማሪ አስተማሪ፣
እጅግ ተበራክተሽ በልጆችሽ ኩሪ።” የመሰሉ መዝሙሮች ይጠቀሳሉ፡፡
ፀሐዬ ዮሐንስ ዘማቹ ጓዴ (የ5ተኛ ወይም የ6ተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ) “ብርሃን ኢትዮጵያ” ትምህርት ቤት መምህሩ የሰጡትን ግጥምና ዜማ አጥንቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ማይክ ጨብጦ ህዝብ ፊት ቀረበ።
ዘመቻው አንድ ፊደል የቆጠረ ትውልድን ይዞ የተጓዘ ታሪካዊ ኩነት ነበር። ወጣቶቹ ከቤተሰብ ተለያይተው ወደገጠሪቷ ኢትዮጵያ ሲጓዙ በሀዘን ሳይሆን በደስታና በመንፈሰ ሙሉነት ነበር።
ታህሳስ 12 ቀን 1967 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የአዲስ አበባ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከየጠቅላይ ግዛቱ ከተወከሉ ተማሪዎች ጋር በጃን ሜዳ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በደማቅ ሠልፍ አደረጉ ።
ፍቅረሥላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደገለፁት 60 ሺህ የሁለተኛ ደረጃና የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ከመምህሮቻቸው ጋር በመላ አገሪቱ በሚገኙ ስድስት ቀጠና ማስተባበሪያ ማዕከላት፣ 57 የክፍለ አገር ማስተባበሪያዎች፣ 517 ምድብ ጣቢያዎችና እያንዳንዳቸው 30 ተማሪዎች ወዳቀፉ ጣቢያዎች ለመላክ ታቅዶ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ መንግሥት ያወጣው ሪፖረት ግን ዘማቾች በ51 ማዕከላትና 397 ጣቢያዎች መዝመታቸውን፤ ቁጥራቸውም 48 ሺ ብቻ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ይላሉ
ፍቅረሥላሴ የሰልፉን ሁኔታ ሲገልፁ “መለዮአቸውን በማውለብለብ በሆታና በጭፈራ “ቪቫ መንግሥቱ” ፤ “ቪቫ መንግሥቱ” እያሉ ሲቃ እየተናነቃቸው በመጮህ አለፉ። አንዳንዶቹ የመንግሥቱን እጅ ለመጨበጥ ወደትሪቡን የሚመጡ ነበሩ። ” ሲሉ ከትበዋል።
ገስጥ ተጫኔም “ነበር” በተሰኘውና ከዘነበ ፈለቀ ብለው ባሳተሙት መጽሐፋቸው የክተት በዓሉን ድባብ እንደሚከተለው ገልፀውታል። “ታህሳስ 12 ቀን 1967 የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ የክተት በዓል በመላ አገሪቱ ተከበረ። ለዘመቻው የተዘጋጁ 60 ሺህ ተማሪዎችን የወከሉ የአዲስ አበባ ዘማቾች በዓሉን ለማክበር በጃንሜዳ ተሰለፉ። ሰልፉን ለመጎብኘትና በዓሉን በጋራ ለማክበር ብርጋዴል ጀነራል ተፈሪ በንቲና ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም በስፍራው ተገኝተው ነበር። ሰልፈኛው በየተመደበበት የዘመቻ ቀጠና በረድፍ እንደቆመ ጃንሜዳን ከምዕራባዊ ጫፍ እስከ ምስራቃዊ ጫፍ ሞልቶት ነበር። ”
በህይወት ግቡ በህይወት
ዘመቻ የምትሄዱ ለዕድገት በህብረት።
እያለ በሆታና በዕልልታ በመሸኘት በሚያልፉባቸው ከተሞችም ምሣና ራት እየጋበዘ ማረፊያ ቦታ አዘጋጅቶ በመቀበል አስተናገዳቸው። በመላ አገሪቱ የገጠር ክፍሎች ተሰማርተው ሥራቸውን ጀመሩ። ገበሬውን በእርሻ ሥራና በዕለት ተዕለት ኑሮው እያገዙት ማንበብና መጻፍን አስተማሩት። ፖለቲካዊ ንቃት እንዲኖረው ለማድረግና መብቱን እንዲጠይቅ አስለጠኑት።
ዘመቻው ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ይፋ በሆነው መግለጫ 5 ሚሊየን 537 ሺህ ገበሬዎች በ19 ሺ 341 ማህበራት መደራጀታቸውን፤ 63 ሺ 500 የፍርድ ሸንጎዎች እና 55 ሺህ የመከላከያ ኮሚቴዎች መቋቋማቸው ተገልጿል። በመሠረተ ልማት በኩልም 264 ክሊኒኮችና 158 ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን፤ 750 የጤና ረዳቶች መሰልጥናቸውና 500 ሺ የቀንድ ከብቶች መከተባቸው ተገልጿል።


Source: Yeneta Tube








No comments yet.