የዶክተሩ፣የአምባሳደሩና የምክር ቤት አባሉ የተከበሩ ቶፊቅ አብዱላሂ 35ኛው የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ የቀሠቀሰው የሞሮኮ አሳዛኝ

- Advertisement -
Sidebar AD

♦️የዶክተሩ፣የአምባሳደሩና የምክር ቤት አባሉ የተከበሩ ቶፊቅ አብዱላሂ 35ኛው የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ የቀሠቀሰው የሞሮኮ አሳዛኝ ትውስታ

♦️የተከበሩ አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ(ዶ/ር)፤ይሄ ስም ለብዙዎቻችን አዲስና እንግዳ አይደለም፤በኢትዮጵያ እግር ኳስ፣በፖለቲካና ከአባይ ባለቤትነት ጋር በሚሠጡት በዕውቀት የተሞላ አስተያየት ከፍ ብሎ ሲነሳ የነበረ ታላቅ ስም ነው፤የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈዴሬሽንን በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነትና በህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢነት በመምራት አሻራቸውን በደማቁ ያሳረፉ፣የስፖርቱን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ትልቅ ባለሙያ ናቸው።

♦️ወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ያውም የሠሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ መሆኑ አንድ የተፈጠረ አጋጣሚን አስታወሠኝና የእጅ ስልኬን አንስቼ በወቅቱ ወደ ሞሮኮ የተጓዘው ብ/ቡድን የቡድን መሪ የነበሩት የተከበሩ አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ(ዶ/ር) ደውዬ ሀሎ አልኳቸው።

♦️የፓርላማ አባል የሆኑትና ፋታ በማይሠጥ ስራ እንደተወጠሩ ንግግራቸው የሚየሳብቅባቸው ዶክተሩ አመታትን የተሻገረ አሳዛኝ የሞሮኮ ገጠመኛቸውን በሞሮኮው አፍሪካ ዋንጫ ወቅት ማንሳቴና ነገሮች መገጣጠማቸው እንዳስገረማቸው ሳይሸሽጉ ገጠመኛቸውን”ኡ እሱ አጋጣሚ የሚረሳ አይደለም”በማለት በርካታ ዓመታት በትዝታ ፈረስ ወደኃላ ጋልበው በማስታወስ ዶክተሩ፣አምባሳደሩና የምክር ቤት አባሉ ቶፊቅ አብዱላሂ እንዲህ አሉ።

♦️”ጊዜውን በትክክል አላስታውሠውም 1995 ወይ 1996 ይመስለኛል ቦታው ደግሞ የአሁኑ የአፍሪካ ዋንጫ ድግስን ሞቅ አድርጋ የደገሠችው ሞሮኮ”

♦️በማለት በሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት የተቀሠቀሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሞሮኮ አሳዛኝ ትውስታቸውን ከትዝታ ማህደራቸው በመምዘዝ ቀጠሉ
“ኡ ከሞሮኮ ጋር ለነበረብን ጨዋታ ያየነውን ፈተና ቃላቶች የሚገልፁት አይደለም፤ ያኔ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሞሮኮ ጋር አንድ ምድብ ውስጥ ነበርን፤ጨዋታችን ዓርብ ቀን ነበር፥ለዓርብ ጨዋታ ዓርብ ዕለት ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነስተን ሞሮኮ ለመግባት ቀጠሮ ይዘናል፤የሞሮኮ ጉዞ ስቃያችንና ፈተናችን የሚጀምረው ከአዲስ አበባ ከመነሳታችን ጀምሮ ነው፤ጉዞአችን በግብፅ ካይሮ ካዛብላንካ በመሆኑ አውሮፕላን ላይ ለመጫን ሻንጣችንን ሸክፈን ኤርፖርት በሠዓቱ ስንደርስ ዛሬም ድረስ ምክንያቱን በማላውቀው ሁኔታ አውሮፕላኑ በመበላሸቱ(በመዘግየቱ)በተባለው ሠዓት አትሄዱም ተብለን ወደኃላ እንድንመለስ ተነገረን፤

♦️ትንሽ ቆይተው መሄድ አለባችሁ ተብሎ ዘግይተን አውሮፕላኑ ላይ ተሳፈርን፤የተሳፈርንበት አውሮፕላንም ሠማዩን ሠንጥቆ እያጓራ ወደ ካይሮ እየተምዘገዘገ 30 ደቂቃ ያህል እንደተጓዘ ሌላ ያልታሠበ ዱብዕዳ ተሠማ፤ወደ ካይሮ የምታደርጉት በረራ አቁማችሁ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ ሲባል ሁላችንም ባለንበት ክው ብለን ቀረን፤አውሮፕላኑ ብልሽት ገጥሞት ነው?ነዳጅ ጨርሶ?ነው የአየር ሁኔታው ለበረራ አስቸጋሪ ሆኖ ነው?ብቻ በአእምሮአችን ያልመጣና ያልተመላለሠ ሃሳብ የለም፤አብዛኛው ሠው ተመለሱ በመባሉ ብቻ ተጨንቆ እንደየዕምነቱ አምላኩን ሲማፀን መመልከት ሁኔታው ምን ያህል ከባድ እንደነበር ይረዳል፤የአውሮፕላኑ ጎማ መሬቱን ሲቆነጥጥና ማረፉ ሲረጋገጥ የነበረው ደስታና የደስታ ጩኸት የተለየ ነበር፤ሁሉም ከአውሮፕላኑ ቶሎ ለመውጣት የነበረው ችኮላና ግፊያ የነፍስ ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደነበር አንደኛው ማሳያ ነበር።

♦️ሁሉም ወደ አዲስ አበባ የተመለስንበትን ለማወቅ ጆሮውን አቁሞ እየተጠባበቀ ባለበት ሠዓት በካይሮ ወደራባት የተደረገው ጉዞ ከአዲስ አበባ ስንነሳ በአውሮፕላኑ ብልሽት ዘግይቶ በመነሳቱ በሠዓቱ መድረስ ስለማይቻል የበረራው መስመር ተቀይሮ በጣሊያን ሮም በኩል መደረጉ ሲነገር ሁሉም ተንፈስ አለ፤ወዲያውኑ ወደ ጣሊያን ሮም እንድንበር ተወስኖ በጥድፊያ ገባን፤አውሮፕላኑም የካይሮውን መስመር ትቶ በጣሊያን ሮም ወደሞሮኮ ጉዞውን ቀጠለ፤ከሠዓታት በኃላ አውሮፕላኑ ሮም ሲደርስ የቪዛ ጥያቄ ሌላው ፈተና ሆኖ ብቅ ቢልም የፌዴሬሽኑ ሠዎች ቀድመው ጨርሠው ስለነበር በፈራነው ልክ ችግር ሳይገጥመን ቪዛውን አገኘን፤ኤርፖርት ውስጥ ሙሉ ቀን ውለን በረሃብና በጉዞ እጅግ ተዳክመናል፤ራባት የደረስነው 11:30-12:00 አካባቢ ስለነበር የጨዋታው ሠዓት የቀረው ከአንድ ሠዓት ያነሠ ጊዜ መሆኑ በዛ ላይ ከራባት ካዛብላንካ 90 ኪ.ሜ መሆኑ ለጨዋታው ላንደርስ እንችላለን በሚል ሁሉም ተጨነቀ፤

♦️የገባነው በጉዞ ተንገላተን፣በረሃብ ተዳክመን በመሆኑ እርስ በራስ ለማውራት አቅም አጣን፤የሆነ ነገር ተገዝቶ እንዳንበላ ችግር ይገጥመናል፣ይርበናል ተብሎ የተያዘ በጀት ስለሌለ ሁላችንም የሚላስ የሚቀመስ አጥተን በረሃብ አለቅን፤በብዙ ፈተና፣ረሃብና መንገላታት ውስጥ ሆነን ሞሮኮ ራባት አየር ማረፊያ ብንገባም ጨዋታው ራባት ሳይሆን ካዛብላንካ ነው ተብለን አረፍነው፤ፈተናውን ልንገላገል ነው ብለን ስናስብ በፈተና ላይ ሌላ ፈተና መጣ፤ፈተናውን ያከበደው ደግሞ ከራባት ካዛብላንካ የ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው መሆኑ ነው፤ይህ ብቻም አይደለም ለጨዋታ የቀረን ጥቂት ሠዓት ብቻ በመሆኑ ፎርፌ መበላታችን ነው ብለን ተጨነቅን።

♦️እኛ ራባት ኤርፖርት ከብዙ ፈተና በኃላ ብንደርስም እዛ የደረስነው ከሞሮኮ ጋር በምንጫወትበት ወይም በሚጀመርበት ሠዓት በመሆኑ ሁላችንንም ረበሸን፤የምንይዝ፣የምንጨብጠውን አጣን፤ከመበሳጨታችንና ከመጨነቃችን የተነሳ እርስ በእርስ አንነጋገርም፣እንደተጣላ ሠው ተኮራርፈናል፤የሞሮኮ ሠዓት እንደዚህ ፈጣን ነው? ብለን እስክንገረም ድረስ ይከንፋል፤እንዳልኩህ የጨዋታው መጀመሪያ ላይ ኤርፖርት በመሆናችን በቃ ለምን እንሄዳለን?ብንሄድም አንደርስም ፎርፌ ነው የምንበላው ብለን ተስፋ በቆረጥንበት ሠዓት አንድ መልዕክት ሞሮኮዎች ስታዲየም ከገቡበት ካዛብላንካ መጣ

♦️”ምን የሚል አትልም?”እኛ ለጨዋታው አንደርስም፣ለፎርፌ ፎርፌ ምንአስኬደን? ብለን በተዘናጋንበት ሠዓት ሞሮኮዎች የጨዋታውን ኮሚሽነር አሳምነው ይሁን በምን አባብለዋቸው እንደሆነ ምክንያቱን ባላውቀውም ባለመገኘታችን ለሞሮኮዎች ሁለት ነጥብና ሁለት ንፁህ ጎል(ያኔ ሁለት ነጥብ ነበር ላሸነፈ የሚሠጠው)ፎርፌ ሠጥተው ከሜዳ ሊወጡ ሲገባ ኮሚሽነሩ ዋና ተሟጋች ሆነው “ኢትዮጵያዊያኖች አውሮፕላን አምልጧቸው ስለሆነ ግድየለም እንጠብቃቸው”በማለታቸው ፎርፌ ሳይሠጥ ወደ ካዛብላንካ 90 ኪሜ በአውሮፕላን ሳይሆን በአውቶቡስ በሞተረኞች ታጅበን የመኪና ጥሩንባ እያስጮሁ በረራ አደረግን፤በአውቶብስ ሄድን ሳይሆን እንደ ንፋስ አበረሩን ብል ይቀላል፤

♦️የሠሜን አፍሪካ ሀገሮች ብልጠትና ተንኮል የገባኝ ሞሮኮዎች አውሮፕላን አምልጧቸው ነው እንጠብቃቸው ያሉት ለካ ለእኛ አዝነው ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም መሆኑን ከሠማሁ በኃላ ነው፤እንዴት አትልም ሞሮኮዎች ከምድባቸው ለማለፍ ብዙ ጎል ያስፈልጋቸው ስለነበርና በርከት ያለ ጎል ከኢትዮጵያ እናፍሳለን ብለው ሂሳብ ሠርተው ስለነበር ሁለት ነጥብና ሁለት ንፁህ ጎል ምን ይጠቅመናል? በሚል ስሌት ነበር ለካ እንጠብቃቸው ያሉት።

♦️ካዛብላንካ ስንደርስ በጉዞ ተዳክመናል፣በረሃብ ጠውልገናል፤ውሃ እንኳን ባለመያዛችን የሚጠጣ ውሃ የሠጡን ራሳቸው ሞሮኮዎች ናቸው፤ብቻ እንዴትና በየት በኩል አድርገው በሞተር አጅበው እያሯሯጡ ወስደውን ራሳችንን የት እንዳገኘነው ታውቃለህ ስታዲየም ውስጥ፤ ስታዲየም ውስጥ፤ከኢትዮጵያ ብዙ ጎል ሸምተን እናልፋለን ብለው ሂሳብ የሠሩት ሞሮኮያዊያን ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ ስታዲየሙን ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልተውት ስታዲየሙን በጩኸት ሊንዱት ምንም አልቀራቸውም፤

♦️የእነሱን ሁኔታ ስናይ ተደናገጥን፤ረሃብ፣የአውሮፕላን አሰልቺ ጉዞና የአውቶቡስ የ90 ኪ.ሜ ጉዞ ተዳምሮበት ድካምና ድንጋጤ እላያችን ላይ እንደሠፈረ አንዲትም ዳቦ፣ውሃም ሳንቀምስ አጣድፈው ሜዳ ውስጥ አስገቡን፤እንደተዳከምን ሞሮኮዎች የሚፈልጉትን ለማሳካት ሶስትና ከዛ በላይ ንፁህ ጎል ያስፈልጋቸው ነበርና ብቻ በምን እንዳደነዘዙን፣እንዴትና ምን አድርገውን እንደሆነ ያን ሁሉ ጎል እንዳዘነቡብን ዛሬም ድረስ ባላውቀውም ትንፋሽ አሳጥተው አራት ጎል አዝንበውብን፣አፍዝዘው አደንዝዘው ሽንፈት አስጎንጭተው የላኩንን ጊዜ 35ኛው የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ አሳዛኙን የምሮኮ ትዝታዬን ቀስቅሶብኝ ላካፍላችሁ ብዬ ይህቺን ለሞነጫጨር ሞክሬያለሁ፤ሞሮኮ ሞሮኮን አንስታብኛለች፤ የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ የቀሠቀሰው የሞሮኮ አሳዛኝ ትውስታዬን በትዝታ ፈረስ ወደ ሞሮኮ አሻግሮ አስታውሶኛል፤መልካም የአፍሪካ ዋንጫ የክትትል ጊዜ ይሁንላችሁ🙏🙏

✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)



Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2