“ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፦እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” (ዮሐ. 1፡29)
#Ethiopia | ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ካከናወናቸው ታላላቅ የትሕትና ተግባራት አንዱ በጥምቀቱ የተገለጠው ነው ። እርሱ መጠመቅ የሚያስፈልገው ሆኖ ሳይሆን የእኛን ጥምቀት ለመባረክና ትሕትናን ሊያስተምረን ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ገሰገሰ፤ ከባሪያው እጅም ተጠመቀ፤ በዚህም ትሕትና ማለት የበላይን ሳይሆን የበታችን ማክበር መሆኑን አስተማረን ። ኃጢአት ወደዚህ ዓለም የገባው በትዕቢት ነበር፤ ጌታችን በትሕትና የጽድቅን መንገድ ከፈተልን ።
ትዕቢት ከገነት ጀምሮ የሰው ልጆች የመውደቂያ ገደል ሁኖ ነበር፤ ቃየን ወንድሙ አቤልን በቅናት ተነሣሥቶ ቢገድለውም የሚፈርድ አምላክን መዘንጋቱ ግን ትዕቢት ነበር፤ ጥቅመ ሰናዖር በጅምር የቀረው በትዕቢት ምክንያት ነበር ። የትኛውም ከፍታ ወደ ዝቅታ የሚለወጠው በትዕቢት ሲሆን ታላላቅ ሥልጣኔዎች ዕድሜ የሚኖራቸው በትሕትና ነው፤ ካልሆነ ግን የሰው ልጆች ስጋት ለመሆን ወዲያው ወደ አውዳሚነት ይቀየራሉ ። ሰዎችን ለመርዳት የመጀመሪያው አቅም ትሕትና ነው ። ትሕትና:- መቆም ፣ ማዳመጥ ፣ ዝቅ ብሎ የሌሎችን ሕመም ማየት ፣ የራስን መውደቂያ በማሰብ ድጋፍ ማድረግ ነው ። ሙሴ በበረሃ የቀረው ትዕቢት የሚመስል ነገር በመናገሩ ነው ። ራስን ከእግዚአብሔር ጋር ማነጻጸር፣ በጸጋ የተቀበሉትን በድካም እንዳገኙ አድርጎ መቍጠር፣ ‹‹እንዴት ሌሎች ይህን ያጣሉ?›› ብሎ መመጻደቅ፣ ተቀብሎ ለመስጠት መሰሰትና የመሳሰሉት በትዕቢት መደብ ላይ ሲገኙ ከሁሉም በላይ አምልኮተ እግዚአብሔርን ማጓደል፣ የፈጣሪን ክብር ለማይገባው መስጠት ደግሞ የትዕቢት አውራ ነው ።
ንጉሥ ዖዝያን ሀብተ መንግሥት ተሰጥቶት ሳለ በትዕቢት ምክንያት ‹‹ሀብተ ክህነቱንስ ማን ይከለክለኛል›› በማለቱና ዕጣን ሊያጥን ወደ መቅደስ በመግባቱ በለምፅ ተቀጣ ። እግዚአብሔር ከብርቱ ንጉሥ ይልቅ ደካማውን ካህን ይወዳል ። ደግሞም ክብራችን ያለው በተሰጠን በመገኘት እንጂ ያልተሰጠንን መፈለግ ትዕቢት ነው ። ክብረ ክህነት በተቃለለበት፣ ካህናት በልጆቻቸው በሚሰደቡበት፣ መስቀልን ቀምቶ አባቶችን ለማባረር በሚመከርበት በዚህ ዘመን የዖዝያን ተግሣጽ ትዝ ሊለን ይገባል ።
ጌታችን ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ቢል ይቻለዋል፤ ነገር ግን በቀጣይ የሚነሡ ነገሥታት መጥታችሁ አጥምቁን ብለው ካህናትን እንዳያዝዙ መሠረት ጣለልን ። የንጉሥ ልጅ ልዑልና ልዕልትም ወደቤተ ክርስቲያን ሄደው ይጠመቃሉና ጥምቀት የትሕትና ትምህርት ቤት ነው ። ትዕቢት መራራቅ ፣ በርቀት መተኮስ ፣ በግምትና በሐሰት የሰውን ስምና ክብር ማርከስ ነው። ትሕትና ግን መሄድ ፣ ቀርቦ ማገዝ ፣ ለወንድምም የስሙ ጠባቂ መሆን ነው ።
ዓለማችን በልዩ ልዩ ጦርነቶች እየታወከች፤ ኃያላን ሲጋፉም ደካማ አገራት እየደቀቁ እንደሆነ እናውቃለን፤ ሰዎች ከምድር ጨርሰው ጨረቃ ላይ ውድድር ከገቡ አንድ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር ቢቃረብም የጦር መሣሪያው ሳይንስ በየጊዜው እየረቀቀ ነው፤ ውጤቱ ግን ሰው ራሱን የሚያወድምበት ዘመን መቃረቡን የሚናገር ነው ። ይህች ዓለም በትዕቢት ምክንያት ክፉኛ ተጨንቃ ምጥ እንደ ያዛት ሴት እየጮኸች ሲሆን እግዚአብሔር አምላክ መሪዎችን አባት ፣ ቤተ ክርስቲያንን እናት አድርጎ ለዚህች ዓለም ሰጥቷልና ለሰዎች ማረፍ ተግተን መሥራት ይጠበቅብናል ።
ጌታችን ለመጠመቅ ወደ ዮሐንስ በሄደ ጊዜ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ የሚጠመቁ ሰዎች ረጅም ሰልፍ ይዘው ስለነበር ‹‹እኔ ጻድቅ ነኝ ልቅደም›› አላለም፤ ደግሞም ‹‹እንዴት በረከሱ መካከል እገኛለሁ?›› አላለም፤ ይልቁንም አዲሱ ሊቀ ካህናት ወደ ብሉይ ኪዳኑ ካህን ጋር እስከሚደርስ ወረፋውን በትዕግሥት ጠበቀ ። ከዚህ ታሪክ ዓለም ብዙ መማር ይችላል፤ እውነተኛ ቅድስና ያለው ሰው ሌላው እንዲቀደስለት ባልንጀራ ለማብዛት ይጥራል እንጂ እንደ ርኵስ አይጸየፍም ። ይልቁንም ወገኖቹን ከእሳት ነጥቆ በማውጣት ለርስተ መንግሥተ ሰማያት ያበቃል።
ሰዎችን ለመርዳት በሰዎች መካከል መሆን አስፈላጊ ነው ። ጌታችን ኃጢአታቸውን ተሸክሞ መሥዋዕት የሚሆንላቸውን ኃጢአተኞች በመካከላቸው ሆኖ የልባቸውን ትርታ፣ የእርስ በርስ የፍርሃት ድምፃቸውን ይሰማ ነበር ። ወደ እውነተኛ ንስሐ ብትመጡ በመካከላችሁ እሆናለሁ ሲለን ይህን አደረገ ። የታደለው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም፡- በተመለከተው ጊዜ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት አስተዋወቀው (ዮሐ. 1፡29) ። ዮሐንስ ስርየትን ያውጅ የነበረው የጥንቱን በግና ፍየል በመሠዋት ሳይሆን እየቀረበ ያለውን የእግዚአብሔር በግ በማሰብ ነበር ። በብሉይ ኪዳን ሰዎች በሚሊየን የሚቆጠሩ በጎችን ቢያቀርቡም መፍትሔ አልተገኘም፤ አንዱ በግ ክርስቶስ ግን ከኃጢአታችን አዳነን ። የሰዎች መላ ችግርን ያዳፍን ይሆናል፣ ችግርን የሚያስወግደው እግዚአብሔር የሚሰጠን መፍትሔ ነው ። በየትኛውም የአገልግሎት መስክ ላይ ሰዎች እንደ አመጣጣቸው መስተናገድ አለባቸው፤ በዕድሜ የሚበልጡንን የምናከብረው በሰውነት ብቻ ሳይሆን በመኖር ስለሚቀድሙን ጭምር ነው ። የሚያየውን አባቱን ያላከበረ የማያየውን አምላክ አከብራለሁ ቢል ይዋሻልና የሚከተሉት የሚቀድሙትን ካላከበሩ እውነተኛ አምልኮ ሊኖር አይችልም ።
መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የሰዎችን ኃጢአት ሲሰማ እየዋለ ግለሰቦች የከበዳቸውን ሸክም ለእርሱ ያሸክሙት ስለነበር በአገልግሎት ብዛት ደክሟልና ጌታችንን ባየ ጊዜ ማረፍንና በጌታ እጅ የሚጠመቅ የመጨረሻው ተጠማቂ ለመሆን ተመኘ ። ጌታችን ግን ዮርዳኖስ የትሕትና ትምህርት ቤት ስለሆነች ከለከለው ። የጌቶች ጌታ ሲሆን በባሪያ እጅ፣ አምላክ ሲሆን በፍጡሩ እጅ ተጠመቀ። የመስቀሉን መልክ አንድም ቀን ትቶት አያውቅምና በዮርዳኖስ ቅዱስ ዮሐንስ በቀኙ ፣ በደለኞች ተነሣሕያን ደግሞ በግራው ይታያሉ፤ እርሱም በመካከላቸው ሆኖ ወደ ራሱ ይስባቸዋል ። በደሉን ላመነ በእግዚአብሔር ዘንድ የበደል እስራት የሚቆረጥበት ምሕረት አለና ትልቁ በደል ንስሐ አለመግባት ነው ።
የናዝሬት ነዋሪዎች አምላክነቱን ቢሰውርባቸው አናጢ አድርገው ስለውት ነበር፤ በዮርዳኖስ ግን መሥዋዕት አቅራቢው ሊቀ ካህናት፣ የአለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ፣ ተወካፌ መሥዋዕትም እርሱ መሆኑ ተገለጠ ። በናዝሬት በእናቱ ቤት ቢሸሸግ ዕለተ ሞቱ ዘገየ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ግን በዮሐንስ ስብከት፤ እግዚአብሔር አብ ከሰማያት ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ ባሰማው ምስክርነት፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ከታየ በኋላ የቀራንዮ ጉዞው ፈጠነ ። በዚህም በተገለጥን ቍጥር መሥዋዕትነት ቅርብ መሆኑን አስተማረን!
ጥምቀት ጅምሩም ወራጁም የድሀ ሀብት ተደርጎ በሚታሰበው ውኃ የሚከናወን ነው ። ጥምቀት ትሕትና ነውና ዝቅ ብለው በሚቀዱት ውኃ መከናወን አለበት ። ሁሉም ሊያገኘው በሚችል ውኃ ምሥጢረ ጥምቀት መመሥረቱም ማንም ሰው በሰበብ እንዳይቀር ለማድረግ ነው። ባለቤቱ በቃልም በተግባርም የቀደሰውንና ያዘዘውን ጥምቀት መናቅ ከድኅነት መጉደልን ያስከትላል ። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ምሥዋዕን አክብራ ወደ ባሕረ ጥምቀት የምትወርደው መሠዊያውና መሥዋዕቱ አይለያዩምና የእግዚአብሔር በግ የሆነው ክርስቶስን ለዓለም ለመስበክ ነው። ስለሆነም በጉ ኃጢአትን ሊያስወግድ መጥቷልና የጥምቀት በዓላችን ምንም ዓይነት የኃጢአት ነቁጥ የማይታይበት፤ ዘፈንና ሥጋዊ መሻት ሁሉ የሚወገድበት በዓል ሊሆን ይገባል ። ኃጢአተኞች ኃጢአተኛን ይገድላሉ፣ በዚህም እግዚአብሔር እንደ እነርሱ መስሎአቸው አበጀህ የሚል ሽልማትን ከአምላክ በመጠበቅ ይስታሉ፤ ጻድቁ ግን ኃጢአትን ይገድላል፤ ለኃጢአተኛውም ይጸልያል፤ በበደል ሸፋኝነትም አምላኩን ይመስላል ።
ማጠቃለያ
በመላው ዓለም በድምቀት የሚከበር ቢሆንም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን ዓበይት ተብለው ከተሰየሙት በዓላተ እግዚእ መካከል በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ አገልጋዮችና ምእመናን በአደባባይ ወጥተው የሚዘክሩት ታላቅ በዓል ነው ። የ2018 ዓ.ም. የጥምቀት በዓልን ስናከብርም ትሕትናን ገንዘብ አድርገን፤ ክህደትን በሃይማኖት፣ ጦርነትን በሰላም፣ መርዶን በብሥራት፣ ኀዘንን በደስታ ለመለወጥ ጠንክረን መሥራት ይጠበቅብናል የሚለው የዘመኑ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክት ነው ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን፡፡
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ (ቆሞስ)
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሓፊ
ጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
Source: GetuTemesgen









No comments yet.