ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለፓርላማ አባልነት በድጋሚ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን በመወከል በባህር ዳር ከተማ ም…

- Advertisement -
Sidebar AD
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለፓርላማ አባልነት በድጋሚ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን በመወከል በባህር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል ተመርጠው ላለፈው አራት ዓመት ተኩል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቆዩት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ በመጪው ምርጫ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ። ዶ/ር ደሳለኝ ራሳቸውን ለምርጫ በዕጩነት ላለማቅረብ የወሰኑት ነጻ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል “ምቹ መደላድል ባለመኖሩ” ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
የፓርላማ አባሉ ይህን የገለጹት፤ የመጪው ምርጫ ተሳትፏቸውን በተመለከተ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ዛሬ ጥር 29፤ 2018 ባሰራጩት መግለጫ ነው። ዶ/ር ደሳለኝ ባለፉት ዓመታት የባህር ዳር ከተማ በመወከል፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዝቡ “ሀቀኛ ድምጽ” በመሆን ማገልገላቸውን በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ለሚካሄደው ሰባተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ የተወዳዳሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በዕጩነት መመዝገብ አለመመዝገባቸውን በተመለከተ “ተደጋጋሚ” ጥያቄዎች ሲቀርብላቸው እንደቆየ ዶ/ር ደሳለኝ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ይፋዊ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ ጥር 1 የተጀመረው የዕጩዎች ምዝገባ ከነገ በስቲያ እሁድ ይጠናቀቃል።
ዶ/ር ደሳለኝ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር በባህር ዳር አሊያም በአዲስ አበባ በዕጩነት እንዲቀርቡ ከ“አንዳንድ ፓርቲዎች” ዕድሉ ተሰጥቷቸው እንደነበር በዛሬው መግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ከሚመሩት አመራሮች ጋር ቅራኔ ያላቸው የፓርላማ አባሉ፤ ዕድሉን የሰጧቸውን ፓርቲዎች በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
@seledadotio
@seledadotio

Source: SeledaPost

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2