የኡቡንቱን ፍልስፍና ወደ ተግባር የሚቀይረው አዲሱ መጽሐፍ ለአንባብያን በቃ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja: በአፍሪካዊ የፍልስፍና እሴቶች ላይ የሚያጠነጥነውና በደራሲ እውነቱ ኃይሉ ዶ/ር ተፅፎ የተዘጋጀው “The Ubuntu Rule of Five” የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሁኔታ ተመረቀ።

“ከፍልስፍና ወደ ዕለታዊ ተግባር’ (From Philosophy to Daily Practice) በሚል መሪ ቃል በተከናወነው የዚሁ መጽሐፍ ምርቃትና የውይይት መድረክ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ ኮሚሽነሮችና ታዋቂ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡

መጽሐፉ “እኔ ነኝ ምክንያቱም እኛ ነን” (I am because we are) በሚለው አንጋፋው የአፍሪካ የኡቡንቱ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ረቂቅ ሀሳቦችን ወደ አምስት ዋና ዋና የዕለት ተዕለት ተግባራት ማለትም፦ ማሰብ፣ መማር፣ መገናኘት፣ ማገልገል እና ማደግ በሚል ቀምሮ ያቀረበ መሆኑ ተገልጿል።

ደራሲው እውነቱ ኃይሉ ዶ/ር በምርቃቱ መርሃ ግብር ላይእንደገለጹት፤ መጽሐፉን ለንባብ ያበቁት የአፍሪካውያን የጋራ መረዳዳትና የአንድነት መገለጫ የሆነውን የኡቡንቱ ፍልስፍና ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ደራሲው አክለውም መጽሐፉ በተለይ ለመሪዎች፣ ለአስተማሪዎችና ለለውጥ ፈላጊ ማህበረሰቦች እንደ መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

መፅሀፉ 135 ገፆች እና 15 ምዕራፎች የያዘ ሲሆን መጽሐፍ አንባቢዎች ሥነ-ምግባራዊ ግንዛቤን፣ የግንኙነት ጥልቀትንና የጋራ ደህንነትን በሚያዳብሩ ትናንሽና ወጥ የሆኑ ድርጊቶች እንዲኖሩ የሚጋብዝ ሲሆን በመድረኩ ላይ በመጽሐፉ ይዘትና በወቅታዊ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምሁራዊ ውይይት ተካሂዷል።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተፅፎ የቀረበው “The Ubuntu Rule of Five” በኢትዮጵያ 700 ብር የሽያጭ ዋጋ ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ ማንኛውም አንባቢ ገዝቶ ማንበብ እንደሚችል ተገልጿል።

እውነቱ ኃይሉ ዶ/ር ከዚህ ቀደም “The Essential Ubuntu” የተሰኘውን መጽሐፋቸውን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም የቀደመ መጽሐፋቸው አሁን ለተመረቀው “The Ubuntu Rule of Five” እንደ መነሻና መሠረት ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነ ተገልጿል።

የቀደመው መጽሐፋቸው በይበልጥ በንድፈ-ሀሳብ እና በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ የኡቡንቱን ምንነት የሚያስረዳ ሲሆን፣ አዲሱ መጽሐፋቸው ያንን የቀደመ እውቀት ወደ ”አምስት የዕለት ተዕለት ተግባራት’ በመቀየር አንባቢው በተግባር እንዲለማመደው የሚያደርግ ተከታይ ስራ እንደሆነ ነዉ የተገለፀዉ።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1