#Fastmereja:በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በአማራጭ የህፃናት ክብካቤ እና ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ አድገው የሚወጡ ወጣቶች፣ ለተደራራቢ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን የብሔራዊ አማራጭ የህፃናት ክብካቤ አድገው የወጡ ማህበራት ጥምረት አስታወቀ፡፡
ጥምረቱ በዛሬዉ እለት ከሚዲያ አካላት ጋር ባካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ፣ ከአማራጭ ህፃናት ክብካቤ እና ድጋፍ አድገዉ በወጡ ወጣቶች ዙሪያ ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎች እና መወሰድ ስላለባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች ሰፊ ማብራሪያ እና የዉይይት መድረክ ተካሂዷል።
የብሄራዊ አማራጭ የህፃናት ክብካቤ አድገዉ የወጡ ማህበራት ጥምረት ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ እንደገለጹት፤ ወጣቶቹ እድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላ ከተቋማቱ በሚወጡበት ወቅት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚገጥማቸው መገለል፣ መድልዎ እና የሲቪል ሰነዶች (የመኖሪያ መታወቂያ) እጥረት ለከፍተኛ እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት ጥምረቱ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን በተለይም የማንነት መታወቂያ አለማግኘት መሰረታዊ የሆኑ የመንግስትና የባንክ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተገልጿል።
እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ወላጅና አሳዳጊዎቻቸውን በተለያየ ምክንያት አጥተው በማሳደጊያ ተቋማት አድገዉ የወጡ መሆናቸዉ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙትና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ አድገው የወጡ ወጣቶች፣ ከማሳደጊያ ሲወጡ የሚገጥማቸውን የህይወት ውጣ ውረድና የስነ-ልቦና ጫና ለሚዲያ አካላት አካፍለዋል።
አብዛኞቹ ወጣቶች የሙያ ክህሎትና የኢኮኖሚ አቅም ሳይገነቡ በድንገት ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ለከፋ ድህነትና ስኬታማ አለመሆን እንደሚጋለጡም ተገልጿል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ”የአማራጭ የእንክብካቤ እና ድጋፍ መውጫ መስፈርት መመሪያ’ ማዘጋጀቱ ተነግሯል። ይህ መመሪያ ህፃናቱ ከማሳደጊያ ሲወጡ በትምህርታቸውና በጤናቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲሁም ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
የጥምረቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ አያይዘውም፤ ሚዲያዎች የእነዚህን ወጣቶች ድምፅ በማሰማት፣ ማህበረሰቡ ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ በመቀየር እና ፖሊሲዎች እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ባካተተ መልኩ እንዲወጡ ግፊት በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥምረቱ በሐምሌ 2016 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በምዝገባ ቁጥር 7316 ፈቃድ አግኝቶ የተቋቋመ አገር በቀል ድርጅት ነው፡፡ ጥምረቱ የተመሰረተው ሰላም ፍሩት፣ የቀድሞ ኤስ.ኦ.ኤስ. ወጣቶች ማህበርኢትዮጰያ እና 4ኬር ሊቨርስ ቻርቲ አሶሲሸን (የግቢ ልጆች) የተባሉ ማህበራት በጋራ በመሆን ነው፡፡



Source: FastMereja









No comments yet.