#Ethiopia | በታሪካዊነቱና በታላቅነቱ የሚታወቀው የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ህንፃ ቤተክርስቲያን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ከማገልገሉ ጋር ተያይዞ በደረሰበት ከፍተኛ እርጅና ምክንያት አጠቃላይ እድሳት ስራ መጀመሩን ተገለጸ።
በዛሬው ዕለት በተሰጠው መግለጫ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ እንዲሁም ሌሎች ብፁዓን አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የገዳሙን ወቅታዊ ሁኔታና የታቀደውን የእድሳት ሥራ የሚመለከት ዝርዝር መረጃ ቀርቧል።
የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ታሪካዊ መሠረት ከአሥረኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ያለው ዘመናዊው ህንጻ በ1954 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባ በመሆኑ ለረጅም ዘመናት ለተፈጥሮ አደጋና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋልጦ ቆይቷል።
በተለይም በህንጻው መዋቅር ላይ የሚታየው ስንጥቅ፣ የጣራው መዝለቅና የዝናብ ውሃ ወደ ውስጥ መግባት ጥንታዊ የሆኑ ሥዕለ አድኅኖዎችንና ንዋያተ ቅድሳትን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጋቸው በመሆኑ አስቸኳይ ርብርብ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህንን ችግር ለመፍታትም መንፈሳዊና ታሪካዊ ግዴታን ለመወጣት የገቢ ማሰባሰቢያና የእድሳት ሥራው በይፋ መጀመሩ ተበስሯል።
ለዚህ ታላቅ የእድሳት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ይውል ዘንድ በጨረታ አሸናፊ ከሆነው አደር ኮንስትራክሽን ጋር ውል የተፈረመ ሲሆን፣ የፋሲል ጊዮርጊስ አማካሪ ድርጅት ደግሞ የህንጻውን ታሪካዊ ይዘት ሳይለቅ የሙያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
የህንጻ እድሳት ሥራው አጠቃላይ 134,000,000 (መቶ ሰላሳ አራት ሚሊዮን) ብር የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሥራው እስከ ሐምሌ 2018 ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ታቅዷል።
ሆኖም ግን በመጪው የሐምሌ ወር የሚከበረውን የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ምዕመናን በበዓሉ ወቅት እንዲገለገሉበት ቅድሚያ የሚሰጣቸው የውስጥ ክፍሎች ዝግጅት እንዲጠናቀቅ በሁለት ፈረቃ ስራው በርብርብ እየተሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ አመራሮችም ይህንን መንፈሳዊ ጥሪ በማስተላለፍ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ምዕመናን፣ በረከቱን ለመካፈልና ይህንን ታሪካዊ ገዳም ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ብጹአን አባቶች ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የእድሳት ሥራው የገዳሙን ጥንታዊ ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲከናወንና የታቀደው የገቢ ማሰባሰቢያ ግብ እንዲመታ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ በማሳሰብ፣ አጠቃላይ ሂደቱ በከፍተኛ ጥንቃቄና እየተሰራ ይገኛል።
የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የህንፃ እድሳት የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች
👉 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ – 1000759706165
👉 አሐዱ ባንክ – 0093543510901
👉 አባይ ባንክ – 18411129 58315015
👉 አቢሲኒያ ባንክ -255602373
👉 አዋሽ ባንክ – 6454
👉 ዳሽን ባንክ – 517116 3880011
👉 አማራ ባንክ – 9900050109805
👉 ሕብረት ባንክ – 1090713234152990
ጌትነት ተመስገን
📷 ከበደ መክብብ
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ


Source: GetuTemesgen









No comments yet.