”ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገባው ስፍራ አግኝቷል ብለ አናስብም” ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ

- Advertisement -
Sidebar AD

* 2ኛው የኦሮሞ ምርምር ማህበር ኮንፈረን እየተካሄደ ነው

#Ethiopia | ​በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር እና የኦሮሞ ምርምር ማህበር (ORA) የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ፣ ማህበሩ ከተመሰረተባቸው ያለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በርካታ ውጤታማ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጹ።

​ማህበሩ በዋናነት የተመሰረተው በኦሮሞ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ እና ፖለቲካዊ ስርዓት ዙሪያ ያሉ የጥናትና የእውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሆነ ተገልጿል። ፕሮፌሰር በቀለ እንደገለጹት፣ እስካሁን ባለው ሂደት ማህበሩ ሰባት መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል።

ከእነዚህም መካከል “ፊንፊኔ፡ ትላንትና ዛሬ” (Finfinne: Past and Present) የተሰኘውና በሶስት ቋንቋዎች (እንግሊዝኛ፣ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ) የተዘጋጀው መጽሐፍ አንዱና ዋነኛው ነው።

​በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እያካሄደ ሲሆን፣ በጉባኤውም ላይ ከኖርዌይ፣ ከጃፓን፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከአሜሪካ የመጡ ምሁራን በአካልና በበይነ-መረብ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ከቀረቡ 24 ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል ግማሽ ያህሉ ተመርጠው በመጽሐፍ መልክ እንደሚታተሙም ተጠቁሟል።

​ፕሮፌሰር በቀለ አክለውም፣ ብዙ ጊዜ የኦሮሞ ታሪክ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ብቻ ተደርጎ የሚወራው የተሳሳተ አመለካከት በምርምር ሊታረም እንደሚገባ ገልጸዋል። ማህበሩ አዳዲስ በሆኑ ስድስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ (ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የነበረ ታሪክ፣ የገዳ ስርዓት፣ ኢኮኖሚና ቢዝነስን ጨምሮ) ጥናቶችን እያከናወነ ይገኛል።

​ይህ የምርምር ማህበር በምሁራን፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በግል ባለሀብቶች ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፣ አላማውም ኦሮሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚገባውን ስፍራ እንዲያገኝ እና ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን አብሮነትና መከባበር ማጠናከር እንደሆነ ተነግሯል።

ኮንፈረንሱ ላይ የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ብርሃኑ መገርሳ ሌንጂሶ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታን ጨምሮ ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ ምሁራን፣የታሪክ ጸሐፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: