የታሪካዊው የቁልቢ ገብርኤል ሕንጻ እድሳት በይፋ ተጀመረ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja:በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታዋቂና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን የመጽናኛና የቃል ኪዳን ስፍራ የሆነው የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሕንጻ፣ በ134 ሚሊዮን ብር ወጪ መጠነ ሰፊ የእድሳት ሥራ እየተከናወነለት እንደሚገኝ በዛሬዉ እለት የገዳሙ አስተዳደር አስታወቀ።

የመሠረት ድንጋዩ በ1884 ዓ.ም የተጣለውና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1954 ዓ.ም በዘመናዊ መልክ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ይኸው ታሪካዊ ሕንጻ፣ ላለፉት 64 ዓመታት መሠረታዊ የእድሳት ሥራ ሳይደረግለት ቆይቷል። በዚህም ምክንያት በተፈጥሯዊ ዕርጅና እና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሕንጻው መዋቅር፣ በጣሪያውና በውስጥ ገፅታው ላይ ከፍተኛ ብልሽት ደርሶበታል።

በዛሬው ዕለት በተሰጠው መግለጫ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ እንዲሁም ሌሎች ብፁዓን በተገኙበት የጋዜጣዊ መግለጫዉ የተሰጠ ሲሆን የገዳሙ አስተዳደር እንደገለጸው፣ በተለይ የጣሪያው ማፍሰስ በጥንታዊ ሥዕለ አድህኖዎችና ንዋየ ቅዱሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ መሠረት በማድረግ እድሳቱ በይፋ መጀመሩን አስታዉቋል።

የእድሳት ሥራው በታዋቂው ‘አዶር ኮንስትራክሽን” (Ador Construction) እና በ”ፋሲል ጊዮርጊስ ኮንሰልቲንግ” (Fasil Giorgis Consulting) እየተመራ የሚገኝ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ 40 በመቶ ደርሷል። ሥራው በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም በቀንና በሌሊት በሁለት ፈረቃ (Two Shifts) እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የእድሳቱ ዋና ግብ ግንባታውን እስከ መጪው ሐምሌ 2018 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤል በዓል ድረስ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በበዓሉ ወቅት የሚኖረውን ከፍተኛ የምዕመናን ፍሰት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የቤተ መቅደሱ የውስጥ ክፍል ቅድሚያ ተሰጥቶት ተጠናቆ ለበዓሉ አገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆንና ቀሪው የውጭ አካል ግንባታ ከሐምሌ በኋላ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ቤተክርስቲያኗ ለዚህ ታላቅ የታሪክና የበረከት ሥራ ምዕመናን በዕውቀት፣ በገንዘብና በማቴሪያል እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረበች ሲሆን ከዋናው ሕንጻ እድሳት በተጨማሪ የቤተልሔም ግንባታ፣ የክርስትና ቤት እድሳት፣ የእንግዶች ማረፊያና የግቢው ማስዋብ ሥራዎችም በበረከት ተሳታፊ መሆን ለሚፈልጉ ክፍት መሆናቸውን አስታውቃለች፡፡

ምዕመናን ድጋፋቸውን በነዚህ የባንክ አካውንቶች ማበርከት እንደሚችሉ ተገልጿል፦

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ – 1000759706165
አሐዱ ባንክ – 0093543510901
አባይ ባንክ – 18411129 58315015
አቢሲኒያ ባንክ -255602373
አዋሽ ባንክ – 6454
ዳሽን ባንክ – 517116 3880011
አማራ ባንክ – 9900050109805
ሕብረት ባንክ – 1090713234152990

ለተጨማሪ መረጃ በስልክ ቁጥሮች
+251 910 05 23 30
+251 911 24 38 71
+251 911 81 15 04
+251 913 82 45 47 ደዉሎ መጠየቅ ይቻላል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2