በ3.5 ሚሊዮን ብር ሸልማት የታጀበው ”የመድን Grand Fight Night” ሊካሄድ ነዉ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja: በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት የውጊያ ስፖርቶችን በአንድ መድረክ ላይ የሚያገናኘው “የመድን Grand Fight Night I” የተሰኘው ዘመናዊ የውድድር መድረክ የፋታችን ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በአድዋ ሙዚየም እንደሚካሄድ በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።

ይህ ታሪካዊ ዝግጅት የሚክስድ ማርሻል አርትስ (MMA)፣ ሟይታይ (Muay Thai) እና ቦክሲንግን (Boxing) በአንድ ላይበማጣመር በሀገሪቱ የስፖርት ኢንዱስትሪ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተስፋ ተጥሎበታል።

ዝግጅቱን ስዌት ቦክስ ጂም፣ ሸጋ ኤቨንትስ እና የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የዝግጅቱ ዋነኛ ስፖንሰር (Title Sponsor) በመሆን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የዝግጅቱ አስተባባሪዎች እንደገለጹት፣ የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያ በማራቶን ያላትን ዝና በውጊያ ስፖርቶችም እንድታገኝ ማስቻል ሲሆን ዝግጅቱ በዘርፉ ያሉ ወጣቶች ያላቸውን ያልተነካ እምቅ አቅም ለዓለም በማሳየት፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ የውድድር መዳረሻ የማድረግ ራዕይ እንዳለዉም ነዉ የተገለፀዉ።

ከዚህም ባሻገር ውድድሩ የጡንቻ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ የስፖርተኞችን ስነ-ምግባር፣ ታታሪነትና ትዕግስት የሚፈተንበት መድረክ እንደሚሆን ታውቋል። ስፖርቱ ለወጣቶች የሥራ ዕድልና መደበኛ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ለማስቻልም ሰፊ ጥረት ተደርጓል።

ለዚህ ውድድር በአሸናፊነት ለሚወጡ ስፖርተኞች በአጠቃላይ ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱ የተገለፀ ሲሆን ይህም ስፖርተኞች በዘርፉ ተስፋ እንዲኖራቸውና ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ማበረታቻ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡

ውድድሩ በዕለቱ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 4፡00 ሰዓት የሚቆይ ሲሆን፣ ታዋቂ ድምፃውያን የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ ዝግጅቱን እንደሚያደምቁትም ተገልጿል።

ይህ ዝግጅት በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጊያ ስፖርት አፍቃሪዎችና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች አዲስ የትውውቅና የውድድር መድረክ በመሆን በታሪክ ማህደር ሰፍሮ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

📷 Zemenu Atalay






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: