የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤክስፖ ተከፈተ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja:የኢትዮጵያ የሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር በመተባበር ያዘጋጀውና “አዲስ አፍሪካ ሪል እስቴት ኤክስፖ 2026” የተሰኘው የመጀመሪያው አህጉራዊ የኤግዚቢሽን መድረክ በዛሬዉ እለት በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም በይፋ ተከፈተ።

ከሚያዝያ 15 እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚቆየው ይህ ኤክስፖ፤ የኢትዮጵያን የሪል ስቴት ዘርፍ ከአህጉራዊ የንግድ ትስስር ጋር ለማስተሳሰር እና አዲስ አበባን በአፍሪካ የዘርፉ የኢንቨስትመንት ማዕከል (Hub) ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ ከተማ በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ማህበሩ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ቢሆነውም በአሁኑ ወቅት ከ100 በላይ አባላትን ማፍራት የቻለ ሲሆን ማህበሩ የአባላቱን መብት ከማስጠበቅ ባለፈ ደንበኞች ጥራት ያለውና በውል በተገባው ጊዜ የሚረከቡትን ቤት እንዲያገኙ የሚያስችል የክትትልና የሙያ ስነ-ምግባር ደንብ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በኤግዚቢሽኑ ላይ የሚሳተፉት የማህበሩ አባል የሆኑ ህጋዊና እውቅና ያላቸው አልሚዎች ብቻ በመሆናቸው፣ ቤት ፈለጊው ማህበረሰብ ካልተገባ እንግልት እንዲጠበቅ እንደሚያደርገዉም ነዉ የተገለፀዉ።

በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ30 በላይ የሪል ስቴት አልሚዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች እና ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተገልጿል ይህም ቤትና የንግድ ቦታ ፈላጊ ማህበረሰብ የተለያዩ አማራጮችን በአንድ ቦታ እንዲያገኝ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ተመልክቷል።

የኤግዚቢሽኑ ሁለተኛ ቀን መርሃ-ግብር የአፍሪካ ሪል ስቴት ማህበር (AFRES) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጉባኤን በኢሊሊ ሆቴል በማስተናገድ የሚቀጥል ሲሆን፣ በዘርፉ የሚሳተፉ ሻጮችን፣ ገዢዎችን እና የግብዓት አቅራቢዎችን በማገናኘት ቀጥተኛ የንግድ ትስስር ለመፍጠር አልሟል።

ከንግድ ትስስሩ ባለፈ፣ በዝግጅቱ ላይ የሚሳተፉ የውጭ ሀገር እንግዶችና ባለሀብቶች በአዲስ አበባ በቅርቡ የተገነቡትን አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችና የኮሪደር ልማቶችን እንደሚጎበኙም በመርሃ-ግብሩ ላይ የተካተተ ሲሆን ይህም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

በመክፈቻው መርሃ-ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአህጉራዊ ማህበሩ የቦርድ አባላት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

📷ከበደ መክብብ






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1