በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ማእቀፍ
ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው
መግቢያ
#Ethiopia | በዚህ ጹሁፋችን በአክስዮን ማህበር አክስዮን የማይተላለፍበትን ምክንያት/ገደቦች/ የምንመለከት ሲሆን እነዚህን ግልጽና አጠር ባለ መንገድ ምክንያቶችን ጭምር በመዳሰስ ለግንዛቤ ለእናንተ የምናደርስ ይሆናል።
1. የአክስዮኖች መተላለፍ አስፈላጊነት
ስለ አክስዮኖች መተላለፍ ገደቦች ከመግባታችን በፊት ስለ አክስዮን መተላለፍ ማንሳቱ የበለጠ ለመረዳት ያስችል ዘንድ ጠቃሚ ነው። የአክስዮኖች መተላለፍ በተለያየ መንገድ የሚከናወን ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በዋናነት በሽያጭ፣በስጦታ፣በውርስ፣በፍርድ ቤት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይህ የአክስዮን መተላለፍ ሂደት የአባላትን፣የማህበሩን ካፒታል ለማሳደግ በግብይቶች መካከል የተለያዩ ካፒታሎችን ሀብቶችን ወደ አክስዮን በመቀየር ሰወች በአንድ ላይ በመሆን ሀብታቸውን በማዋጣት ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩበት ፣ ነጻ እና አስተማማኝ የሆነ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ የአክስዮን መተላለፍ ትልቅ ሚና አለው።
2. በአክስዮን ማህበር የአክስዮን ዝውውር ገደብ
የአክስዮን ዝውውር በንግድ ህግ ቁጥር 276/1/ የሚገደብ መሆኑን ይደነግጋል።
አንቀጽ 276/1/ በአክሲዮኖች ዝውውር ላይ የሚደረግ ገደብ
በማኅበሩ መመስረቻ ጽሑፍ ወይም በባላክሲዮኖች አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በአክሲዮኖች ዝውውር ላይ ገደብ ሊደረግ ይችላል በማለት ተደንግጓል።
2.1 በመመስረቻ ጽሁፍ የሚደረግ የአክስዮን ዝውውር ገደብ
አክስዮን ማህበሩ በመመስረቻ ጹሁፉ ላይ የአክሲዮን ፈራሚዎች ተሰብስበው በሚመሰርቱት የመመስረቻ ጹሁፍ ላይ የአክስዮን ዝውውርን አስመልክቶ ተስማምተው የሚያጸድቁት ነው።
2.3 በድንገተኛ/አስቸኳይ/ ጠቅላላ ጉባኤ
ምንም እንኳን በመመስረቻ ጽሁፍ ላይ የተፈለገውን የአክስዮን ዝውውር ገደብ ያልተገለጸ እንደሆነ ድንገተኛ የጠቅላላ ጉባኤ በመጠራት የአክስዮን ዝውውር ገደብ መወሰን ይችላል።
ነገር ግን አክስዮን የማስተላለፍ ገደብ በመመስረቻ ጽሁፍ ወይም በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ አማካኝነት ሊፈጠር ይችላል
2. 4. የአክስዮን መተላለፍ ገደቦች አላማ
የአክስዮን መተላለፍ ገደብ የሚበጅለት የአክስዮን ማህበሩን እና አባላትን አላማና ጥቅም መጠበቅ ሲባል በዘፈቀደ አክስዮን እንዳይተላለፍ በንግድ ህጉ በመጠበቅ ሉጋም ማበጀት ወሳኝ በመሆኑና ይህም የከፋ ጉዳትን እንዳያስከትል ማህበሩ የተቋቋመለትን አላማ ለመጠበቅ ነው። የአክስዮን ዝውውር እና ገደብን አስመልክቶ አጠቃላይ ሀሳቡን ለመረዳት ይህን በተመለከተ የሚደነግገውን አንቀጽ ሙሉውን መረዳት አስፈላጊ ሲሆን እንደሚከተለው ሰፍሯል።
አንቀጽ 276 በአክሲዮኖች ዝውውር ላይ የሚደረግ ገደብ
1) በማኅበሩ መመስረቻ ጽሑፍ ወይም በባላክሲዮኖች አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በአክሲዮኖች ዝውውር ላይ ገደብ ሊደረግ ይችላል፤
2) አክሲዮኖች ከመተላለፋቸው በፊት የዳይሬክተሮች ቦርድ ፈቃድ እንዲጠየቅ በመመስረቻ ጽሑፉ ወይም በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሊወሰን ይችላል፡፡ ሆኖም ውሳኔው ውጤት የሚኖረው፡-
(ሀ) አክሲዮኖችን መልሶ የመግዛት የቅድሚያ መብት ለማኅበሩ ወይም ለባለአክሲዮኖቹ የተጠበቀ ከሆነ እና
(ለ) መብቱ የሚሰራበት ሁኔታና የአክሲዮኖቹ መግዣ ዋጋ ቀድሞ የተወሰነ ከሆነ፤ ነው፤
3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) መሰረት የሚደረግ ገደብ አክሲዮን ማስተላለፍን የሚከለክል ወይም አክሲዮን ለማስተላለፍ በሚፈልገው ባለአክሲዮን ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ መሆን የለበትም፤
4) ቅድሚያ የመግዛት መብት የተሰጠው ለማኅበሩ ከሆነ የአክሲዮኖቹ ዋጋ የሚከፈለው ከመጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ወይም ከተጣራ ትርፍ ላይ መሆን አለበት።
ከዚህ አጠቃላይ ድንጋጌ ሀሳብ መረዳት የሚቻለው የአክስዮን ዝውውር ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባ መሆኑን ነው። ከድንጋጌዎቹ ሀሳቦችን በመውሰድ እንግለጽ።
በአንቀጽ አንድ ላይ የአክስዮን ዝውውር ላይ ገደብ ሊጣል እንደሚችል የተደነገገ ሲሆን ይህም በመመስረቻ ጹሁፍ ወይም በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሊገደብ እንደሚችል ተደንግጓል። ይህ የአክስዮን ዝውውር ገደብ በባስፈለገ ጊዜ በዚህ መሠረት መሆኑን ነው።
በአንቀጽ ሁለት ላይ እንደተመለከተውም አክስዮኖች ከመተላፋቸው በፊት የዳይረክተሮች ቦርድ መጠየቅ እንዳለበት አስፈላጊ ነው ተብሎ ከታመነበት በመመስረቻ ጹሁፍ ወይም በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሊወሰን እንደሚችል ተደንግጓል። ይህም በዚህ መልክ የአክስዮን ዝውውሮችን መገደቡ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ተብሎ በልዩ ሁኔታ ሲታሰብ ነው።
ሌላው በአንቀጽ ሶስት እንደሰፈረው በአንቀጽ አንድ እና ሁለት ላይ የተቀመጠው የአክስዮን ዝውውር ገደብ መሠረታዊ በሆነው የአክስዮን ማስተላለፍ እና የባለ አክስዮኖችን ጥቅም ጉዳት ውስጥ የሚከት ሊሆን እንደማይገባ ይደነግጋል። ሊደረግ የሚችለው ገደብ እንጂ ሊከለክል የሚችል አይደለም። ይህ ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል። ይህ በቀላሉ ያለ በቂ ምክንያት የአክስዮን ዝውውር እንዳይገደብ ነው።
ሌላው በአንቀጽ አራት ላይ የተደነገገውን ብንመለከትም የዝውውር ገደብን የሚገልጽ ሲሆን የአክስዮን ቅድሚያ የመግዛት መብትን በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ቅዳሚያ መብት ለማህበሩ በመመስረቻ ጹሁፍ ወይም በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሊወሰን ይችላል። ይህን ከንግድ ቀጥሩ 276/1/ እና /2/ ጋር አንድ ላይ መመልከትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ማህበሩ ቅድሚያ ከተሰጠው የአክስዮኑ ዋጋ የሚከፈለው ከመጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ወይም ከተጣራ ትርፍ ላይ መሆን እንዳለበት ይደነጋል። ይህ ማለት ባለ አክስዮኖች ከራሳቸው ሌላ ግዴታ ውስጥ የሚከት አይደለም።
4. የጹሁፉ ማጠቃለያ
የአክስዮን ዝውውር በመርህ ደረጃ የሚፈቀድ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ብቻ በመመስረቻ ጹሁፍ ወይም በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ሊገደብ ይችላል።
ማጣቀሻዎች/References/
1. የንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/2013
2. ፍቃዱ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ የኩባንያ ህግ
ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው 0929101037, 0983337690
Source: GetuTemesgen









No comments yet.