#FastMereja I ሻምፒየንስ አካዳሚ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን “ኦቲዝም እና ሰብአዊነት እያንዳንዱ ሕይወት ዋጋ አለው!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ። አካዳሚው በአንድ ወቅት አካታች ትምህርትን (Inclusive Education) ለመተግበር በወሰደው ውሳኔ ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን እስከ ማስወጣት የደረሰ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ያስታወሰ ሲሆን፣ ዛሬ ግን ለተማሪዎቹ ስኬትና ለአካታች ትምህርት ተምሳሌት መሆኑን አብስሯል።
በመድረኩ እንደተገለፀው አካዳሚው ከዓመታት በፊት “አካታች ትምህርት” እንግዳ በነበረበት ወቅት የጀመረው ጉዞ ፈታኝ ነበር ተብሏል። በተለይም ኦቲዝም ካለባቸው ልጆች ጋር ልጆቻችንን አብረን አናስተምርም በሚሉ ወላጆች ትምህርት ቤቱን ጥለው የመሄድ አስቸጋሪ ወቅት ቢኖርም፣ ተቋሙ በራዕዩ በመጽናቱ ዛሬ ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት ስኬቶች የተመዘገቡ ሲሆን ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የሚኒስትሪ ፈተናን በብቃት አልፈው ወደ ቀጣይ ክፍል እንዲሸጋገሩ ተደርጓል። ተማሪዎቹ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቁ ሆነው ተገኝተዋል። መደበኛ ተማሪዎች ከልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ጋር አብረው በመኖራቸው ሌሎችን የመቀበልና የመደገፍ የህይወት ዘመን እሴት መቅሰማቸው ተጠቅሷል።
አካዳሚው አሁን ካለው ውጤት በመነሳት ወደፊት አካታች የሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ኮሌጅ የመመስረት ራዕይ እንዳለው ይፋ አድርጓል።
በመጨረሻም፣ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በተፈጥሯቸው ታማኝ፣ ስርዓትን የሚከተሉና ለማጭበርበር የማይመቹ በመሆናቸው፣ ለሀገሪቱ የፀረ-ሙስና ትግል ትልቅ ተስፋዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ የተገለጸው ሃሳብ በዕለቱ ልዩ ትኩረት ስቧል። ማህበረሰቡም ከርህራሄ ባለፈ ወደ ተግባርና ወደ መከባበር እንዲሸጋገር ጥሪ ቀርቧል።



Source: FastMereja









No comments yet.