በኦቲዝም ላይ የምትሰሩ ባለሙያዎችና ተቋማት ወይም ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ያላችሁ ወላጆች በሙሉ !!

- Advertisement -
Sidebar AD

አንድ ጊዜ ስሙኝ

አውቃለሁ ፣ እዚህ ሃገር ብዙ የሚያማርሩ የትኩረት ማጣት ፈተናዎች አሉ። በተለይ ስለኦቲዝም መንግሥትን ጨምሮ የግል ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ፣ እንዲሁም ሚዲያዎች ብዙም ግድ አይሰጣቸውም ። የችግሩን ሥፋት እና የስርጭቱን መጠን ገና በውል አልተረዱትም። ህመሙ በራቸውን ካላንኳኳ የማይነቁ ብዙ ናቸዉ። ተከታታይ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ እሙን ነው።

ነገር ግን በማስ ሚዲያ፣ በማሕበራዊ ሚዲያም ይሁን በምታገኙት መድረክ ሁሉ ስለ አቲዝም ለማውራት ዕድል ስታገኙ “ኦቲዝም እርግማን አይደለም ” የሚል አንድ ቃል ብቻ በመደጋገም የኦቲዝምን ምንነት ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ እንደማይቻል ተረዱ ።

ኮሚዩኒኬሽን የራሱ ሣይንስ አለዉ። ህዝቡን ላስተምር፣ ላስገንዝብ እያሉ መክሰስና መውቀስ በሰሚው ዘንድ መሰልቸትን ያመጣል :: ገና በአግባቡ ኮሚዩኒኬት ያልተደረገውን ኦቲዝምን የሚያክል ትልቅ ማህበራዊ ችግር ገና በጠዋቱ የተሰለቸ ርዕስ አታድርጉት።

አንድ ቃል ሲደጋገም ይቸካል ፣ ይሰለቻል።” አቲዝም እርግማን አይደለም ” ማለት ብቻ ስለ አቲዝምን ማስረዳት አይደለም ። “እሺ ምንድነው ? “ለሚል ጥያቄ የተዘጋጀ መልስ ያስፈልጋል።

ኦቲዝም ላይ እየሠራችሁ ያላችሁም ሁኑ ወይም ወላጆች ስለ ኦቲዝም ለማውራት ከመነሣታችሁ በፊት ስለኦቲዝም በቂ ግንዛቤ ሊኖራችሁ ይገባል። ግልፅ ያለና ሣይንሳዊ መልስ መስጠት አለባችሁ ። ይህን ለማድረግም ኦቲዝምን በቅጡ ማጥናትና ዓለም የተሰማማበትን ትርጉሙን ማወቅ አለባችሁ።

ዛሬ እናንተ ዘወትር እንደመፈክር የምትደጋግሙት ” ኦቲዝም እርግማን አይደለም” የሚል ቃል በሆነ ጊዜ እጅግ በጣም አስፈላጊ የማንቂያ ደወል ነበር። ገና ስለ ኦቲዝም ምንም ግንዛቤ ባልነበረበት ከዛሬ 10 ዓመታት በፊት ማንኛውም የዐዕምሮ ዕድገት ሁኔታ (neurodevelopmental condition ) ከመናፍስት እና ከእርግማን ጋር ይያያዝ ነበር። አሁንም ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም።

ነገር ግን አሁን አሁን በአብዛኛው ይህ አመለካከት እየተቀየረ ነው። በተለይ “ኦቲዝም እርግማን ነዉ” የሚል ዕምነት ያለዉ ሰው ቍጥር አሁን አሁን ያን ያህል የገነነ አይደለም።

በኔ ዕምነት አሁን ህዝቡ ጋር ያለዉ ክፍተት እዚህ ሃሣብ ተሻግሮ ኦቲዝም ምን ማለት እንደሆነ አለመገንዘብና ኦቲዝም ራሱ ምን እንደሆነ አለማወቅ ነዉ። ስለዚህ የማያውቀውን ኦቲዝምን “እርግማን አይደለም” እያሉ ልክ ህዝቡ ሁሉ እርግማን አድርጐ እንደሚቆጥረዉ ማወጅ ትልቅ ፍረጃና ስህተት ነው።

ይህ “ኦቲዝም እርግማን አይደለም” የሚል ወቅቱን ያላገናዘበና ከድጋፍ ይልቅ ወዳልተፈለገ ሽሽትና ሥልቹነት የሚመራ ቃል “ስለኦቲዝም እንወቅ” በሚል መሪ ቃል መተካት አለበት።

ኦቲዝም የዕምሮ ዕድገት ሥርዓት መዛባት ( Neuro developmental disorder ) መሆኑ፣ ህመምም በሽታም አለመሆኑ፣ ከኛ በተለየ መንገድ ዓለምን በልዩነት መረዳት መሆኑ ፣ በራስ ዓለም ውስጥ መኖርና ነገሮችን ሁሉ በራስ መንገድ መረዳት መሆኑ ወዘተ ከነመገለጫውና ይህንን ለማሻሻል ከሚሠጠው ህክምና (ቴራፒ) ጋር አዛምዶ መግለፅ በቂ ነው።

ህዝብ እንዲያውቅ በር መክፈት እንጂ በተሰለቸ ቃል “ኤጭ!” ብሎ በር እንዲዘጋ ከማድረግ እንቆጠብ ። ይህ ሴንሴቲቭ የሆነ መረጃ ወደህዝብ የሚደርስበት መንገድ አሠልቺ እንዳይሆንና የምንፈልገው የአመለካከትም ይሁን የዕውቀት ክፍተት ሳይደፈን እንዳይቀር መጠንቀቅ አለብን።

ስታወሩ በዕውቀት ይሁን!
በርቱ!!



Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: