ተቋማት ታማኝነትን መርህ አድርገው ከሰሩ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ኮሜርሻል ኖሚኒስ ህያው ምሳሌ መሆኑን ተገለጸ

- Advertisement -
Sidebar AD

“60ዓመታትን በታማኝነት” የኮሜርሻል ኖሚኒስ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ

#Ethiopia | በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆኑ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አንዱ የሆነው ኮሜርሻል ኖሚኒስ (Commercial Nominees)፣ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሀዋሳ ከተማ ደማቅ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አካሂዷል።

መድረኩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የኮሜርሻል ኖሚኒስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኮማንደር ጥላሁን ፀጋዬ እንደተናገሩት ኮሜርሻል ኖሚኒስ በሀገር ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ስኬታማ ሥራ እየሰራ መሆኑ ጠቅሰው በተለይም በጥበቃ አገልግሎት ዘርፍ የማይረሳ አሻራ እያኖረ እንደሚገኝ አስታውሰዋል። ሩጫው በሀዋሳ መካሄዱም ተቋሙ በከፍተኛ የዕድገት ጎዳና ላይ ለምትገኘው ለዚች ውብ ከተማ ያለውን አጋርነት ለማሳየት ታሳቢ መደረጉን ገልጸዋል።

የኦሎምፒክ እና የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ አትሌት ገዘሀኝ አበራ በውድድሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ ባስተላለፈው መልእክት፣ ኮሜርሻል ኖሚኒስ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በታማኝነትና በጽናት ተጉዞ ለዚህ ስኬት መብቃቱን ገልጿል። አትሌቱ አክሎም፣ “እያንዳንዱ ተቋምም ሆነ ግለሰብ ታማኝነትን መርሁ አድርጎ ከሰራ ስኬታማ መሆን እንደሚችል ኮሜርሻል ኖሚኒስ ህያው ምሳሌ ነው” ብሏል።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው የኮሜርሻል ኖሚኒስን የ60 ዓመት ጉዞና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ጉልህ ሚና አድንቀዋል። ከንቲባው በከተማዋ የተጀመሩ ሰፋፊ የልማት ስራዎችን በስኬት ለማጠናቀቅ እንደ ኮሜርሻል ኖሚኒስ ያሉ ጠንካራ ተቋማት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተቋሙ የጀመረውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በጎዳና ሩጫ ውድድሩ በወንዶች ለማ መለሰ እና ኢያሱ እሽኔ ከሲዳማ ፖሊስ 1ኛ እና 2ኛ እንዲሁም አረጋ ከበደ ከሀዋሳ ፕሮጀክት 3ኛ፤ በሴቶች ወርቅነሽ ሾዴ እና ዘሪቱ ጣሂሮ ከሲዳማ ፖሊስ 1ኛ እና 2ኛ እንዲሁም ሰላማዊት ለገሰ ከሀዋሳ ፕሮጀክት 3ኛ በመውጣት የተዘጋጀላቸውን የገንዘብ እና የሜዳሊያ ሽልማት ተቀብለዋል። ኮሜርሻል ኖሚኒስ የሀዋሳ ከተማ ዕድገትን ከመደገፍ አንጻር የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አብርክቷል፡፡

‎በተጨማሪም ለሩጫ ውድድሩ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት ሠርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

‎የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ሰላም ውሃ እና ዋንዛ ኤክስፕረስ የሩጫ ውድድሩን ስፖንሰር ያደረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የኮሜርሻል ኖሚኒስ እና የሌሎች ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

ይህ የታሪካዊ የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የኮሜርሻል ኖሚኒስን የ60 ዓመታት ስኬታማ ጉዞ ከማብሰሩም በላይ፣ በከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉ የውድድሩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1