⚫ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲሆን የተለገሰ 6,594 የቤት ክዳን ቆርቆሮ ተሸጦ ለግል ጥቅም ውሏል ፤ 3,702,466.67 ብር ነው ተሽጦ የተበላው።
የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ዳዊት ገበየሁ እና የግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኃላፊ የነበሩት አቶ ገደኖ ካዋይታ ላይ የፍርድ ውሳኔ ማሳለፉን የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሀባ ቀውያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ ” የመንግስትን የሥራ ኃላፊነት በማይመች አኳኋን መምራት እና የሙስና ወንጀል ” ጥፋተኛ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አሳውቀዋል።
ተከሳሾቹ በ2014 ዓ.ም በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲሆን ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የተለገሰውን 6,594 የቤት ክዳን ቆርቆሮ ሸጠው ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በማስረጃ መረጋገጡን አቶ ሙሀባ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስረድተዋል።
ተከሳሾች ለግል ጥቅማቸው ያዋሉት ሀብት ግምቱ ብር 3,702,466.67 (ሶስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሁለት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ስልስት ብር ከስልስ ሰባት ሳንቲም) መሆኑን ጠቅሰው ፤ የተገኘው ጥቅምና በህዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት እንዲሁም የወንጀሉ ዓላማ ከባድ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ግምት ውስጥ ማስገባቱን ገልጸዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ፍርድ ቤቱ በመመሪያው መሠረት ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ50,000 ብር መቀጮ እንዲቀጡ መነሻ ቅጣት ወስኖ ነበር።
ይሁን እንጂ ተከሳሾቹ ፦
– ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የሌላቸው፣
– የቤተሰብ አስተዳዳሪና ለረዥም ጊዜያት ያገለገሉ በመሆናቸው፤
– በተለይ 1ኛ ተከሳሽ “እምርታ” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ የነበሩ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው ሦስት የቅጣት ማቅለያዎች መያዛቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አብራርተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤት የሚከተለውን የመጨረሻ ውሳኔ ማስተላለፉን አቶ ሙሀባ ቀውያ ገልጸዋል።
1ኛ ተከሳሽ አቶ ዳዊት ገበየሁ ፦ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ከሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በሚቆጠር በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 20,000 የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ፤
2ኛ ተከሳሽ አቶ ገደኖ ካዋይታ ፦ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ከመስከረም 14 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሚቆጠር በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 20,000 የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።
በተጨማሪም ተከሳሾቹ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትን ብር 3,702,466.67 ለመንግስት በጋራ እንዲመልሱ መወሰኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
አቶ ዳዊት ገበየሁ በዚሁ ፍ/ቤት በሌላ የወንጀል መዝገብ የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በ7 ዓመት ጽኑ እስራትና በ5,000 ብር መቀጮ ተፈርዶባቸው የነበረ መሆኑን አቶ ሙሀባ ገልጸው፤ ሁለቱም የወንጀል ቅጣቶች ተደምረው ተከሳሹ በአጠቃላይ በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በ25,000 ብር የገንዘብ መቀጮ የሚቀጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
@tikvahethiopia
Source: Yeneta Tube









No comments yet.