ታዋቂው የትግርኛ ሙዚቃ ድምጻዊ ፀጋዘአብ ገ/ስላሴ “ንጉስ ዳግማይ ንጉስ” የተሰኘውን 4ኛ የሙዚቃ አልበሙን የፊታችን ሐሙስ ሚያዝያ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለታዳሚ እንደሚያበቃ አስታወቀ።
ድምጻዊው ዛሬ በካፒታል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አልበሙ በፍቅር፣ በማህበራዊ ህይወትና በባህል ላይ ያተኮሩ 12 ስራዎችን ማካተቱን ገልጿል።
ይህ አልበም በጥራትና በስፋት ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ የሁለት ዓመታት ጊዜን የፈጀ ሲሆን ለዝግጅቱም ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።
በአልበሙ ውስጥ ከሚገኙት 12 ትራኮች መካከል የአንዱ ዜማ የህዝብ ሲሆን ቀሪዎቹ 11 ስራዎች ግጥምና ዜማቸው በራሱ በድምጻዊ ፀጋዘአብ ገ/ስላሴ የተሰናዱ ናቸው።
በርካታ አንጋፋና ወጣት የትግርኛ ሙዚቃ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ይህ ስራ ለአድማጮች የሚደርሰው በራሱ በድምጻዊው “ናዶና” (Nadona) የዩቲዩብ ቻናል እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የዲጂታል የሙዚቃ መተግበሪያዎች አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል።
ድምጻዊ ፀጋዘአብ ገ/ስላሴ ከዚህ ቀደም ባወጣው “እምበይተይ” በተሰኘው ነጠላ ዜማው በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማትረፉ ይታወሳል።
አዲሱ አልበሙም ያንን ተወዳጅነት ይበልጥ እንደሚያጠናክርለት ይጠበቃል።
ይህንን የአልበም ምርቃት መርሃ ግብር ኤርሚ ኤቨንት ከዳይናሚክ ኢንተርቴይመንት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።



Source: Yeneta Tube








No comments yet.