(መላኩ ብርሃኑ)
#Etማሣሠቢያ – ይህ ጽሁፍ ትንሽ ረዘም ይላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለማወቅ ፍላጎት ያላችሁ ብቻ አንብቡት፡፡ ሌሎች ጊዜያችሁን አትፍጁ፡፡
ማምሻዬን ዜና ስቃርም AllISRAELNEWS.COM ላይ የሰፈረው “Finding the Ark of the Covenant: A Geo-theological ‘atomic bomb’” የሚል ርዕስ ሳበኝና አነበብኩት፡፡
( ፍላጎት ያላችሁ ወዳጆች ይህን አርቲክል ከላይ በፃፍኩት ርዕሰ ጉግል ላይ ሰርች አድርጋችሁ እንድታነቡት እመክራለሁ )
ይህ በቅርቡ በይሁዳ ቪ ፍራንክ (Yehuda V. Frank) በተባለ ጸሃፊ የተጻፈው አርቲክል ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታች ዘንድ ያለውን የጥንት እምነትና ታሪክ የሚፃረር አዲስ መላምት ይዞ ነው የመጣው፡፡
የቃል ኪዳኑ ታቦት ፍለጋ እና አዲሱ አወዛጋቢ ዘገባ!
ይህ ዘገባ የቃል ኪዳኑ ታቦት (ታቦተ ጽዮን) መገኘት በሃይማኖታዊና ፖለቲካዊው ዓለም ላይ ድንገት ሊፈነዳ እንደሚችል ደ “ጂኦ-ቲዎሎጂካል አቶሚክ ቦምብ” አደርጎ በማቅረብ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ነገር ግን ዘገባው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እጅግ እንግዳ የሆነና ታሪካችንን የሚክድ አዲስ አቅጣጫ ይዞ ነው የመጣው።
የዘገባው ዋና ዋና ነጥቦች፦
ጽሑፉ ታቦተ ጽዮን አሁንም ባለበት በኢየሩሳሌም በመቅደስ ተራራ (Temple Mount) ሥር በሚገኙ ምስጢራዊ ዋሻዎች ውስጥ ተቀብሮ ይገኛል የሚል ድምዳሜ ላይ ያዘነብላል።
ሳይንቲስቶች መሬት ሳይቆፍሩ የድንጋይ ንጣፎችን አልፎ ማየት የሚችል Muon Tomography የሚባል አዲስ የራጅ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ታቦቱን ለማግኘት እየተዘጋጁ እንደሆነ ይጠቁማል።
በሰሜን እስራኤል (ሺሎ) እየተዘጋጁ ያሉ አምስት ቀይ ላሞች (Red Heifer) ለሦስተኛው ቤተ መቅደስ ግንባታና ለክህነት አገልግሎት መታደስ እንደ ምልክት እየታዩ መሆኑን ያብራራል።
የታቦቱ መገኘት ለዓለም ሰላምን ሊያመጣ ይችላል ወይም ደግሞ የመጨረሻውን የ”አርማጌዶን” ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት ያነሳል።
ዘገባው ለምን አወዛጋቢ ነው አልኩ?
ይህ ጽሑፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች “ታቦተ ጽዮን በአክሱም ማርያም ጽዮን ትገኛለች” የሚለውን ጥልቅ እምነት ሙሉ በሙሉ ችላ ይላል።
ታቦቱ በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱንና ላለፉት ሺህ ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ መጠበቁን እንደ ተረት ይቆጥረዋል።
ታዋቂው ተመራማሪ ግርሃም ሐንኮክ “The Sign and the Seal” (የቃል ኪዳኑ ታቦት ፍለጋ) በሚለው መጽሐፉ ታቦቱ በኢትዮጵያ ስለመኖሩ ያቀረበውን ሳይንሳዊና ታሪካዊ መላምት ይህ ዘገባ ውድቅ ያደርገዋል።
የታቦቱ መገኘት ጥቂት ሜትሮችን በቴክኖሎጂ ከመፈተሽ ጋር ብቻ የተያያዘ አድርጎ ማቅረቡ፣ ነገሩ ያለውን መንፈሳዊና ምስጢራዊ ጥልቀት ያቀለለው ይመስላል።
የታቦተ ጽዮን ፍለጋ — በጂኦ-ፖለቲካ ስጋት እና በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናት መነጽር ሲታይ
ይህ አዲስ የ“እስራኤል ኒውስ” ዘገባ ታቦቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ነው ብሎ መደምደም ብቻ ሳይሆን፣ ፍለጋው የዓለምን ሠላም ሊያናጋ የሚችል “የቲዎሎጂ አቶሚክ ቦምብ” ነው ይለዋል። እስቲ ጉዳዩን ከሁለት አቅጣጫ እንየው፡
የፖለቲካው ስጋት፡ “የመጨረሻው ጦርነት መቀስቀሻ?”
ዘገባው የታቦቱን መገኘት ከሦስተኛው ቤተ መቅደስ ግንባታ ጋር ያገናኘዋል። ይህ ደግሞ በሦስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች (ክርስትና፣ እስልምና እና ይሁዲነት) መካከል ውጥረት ፈጥሮ ነገሩን ወደ አደገኛ ደረጃ ሊያሸጋግር የሚችል ይመስለኛል፡
ለምሳሌ ለአይሁድ እምነት፡ የታቦቱ መገኘት የመሲሁ መምጣት እና የመቅደሱ መታደስ ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
ለእስልምና እምነት ደግሞ ታቦቱ በኢየሩሳሌም መገኘቱ “መህዲ” ለተባለው መሪያቸው መምጣት ምልክት እንደሆነና ይህም ዓለም አቀፍ የእስልምና ሥርዓትን እንደሚያሰፍን ያምናሉ ይላል።
ይህ የፍለጋ እቅድ በኢየሩሳሌም የቅዱሳን ስፍራዎች (Temple Mount) ላይ ላለው ግጭት ቤንዚን ማርከፍከፍ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ጽሑፉ እንደሚለው፣ ፍለጋው ወደ “አርማጌዶን” (የመጨረሻው የጥፋት ጦርነት) ሊያመራ የሚችል የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍንዳታ ነው።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ምላሽ፡ “ታቦቱ የት ነው ያለው?”
ዘገባው ታቦቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ተቀብሮ ቀርቷል ቢልም፣ የኢትዮጵያ ጥንታውያን ድርሳናትና ታሪክ ግን ይህንን ፈጽሞ አይቀበሉም። እንደ ክብረ ነገሥት ያሉ የታሪክ መጻሕፍት ታቦቱ ከ3,000 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ በማስረጃ ያስረዳሉ፡
የቀዳማዊ ምኒልክ ጉዞ፡ ንግሥተ ሳባ ከንጉሥ ሰሎሞን የወለደችው ልጇ ምኒልክ አባቱን ለመጠየቅ በሄደበት ወቅት፣ ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን ታሪካችን ያረጋግጣል።
ታቦቱ ከአክሱም በፊት በጣና ቂርቆስ ለ800 ዓመታት፣ ከዚያም በተለያዩ የሰሜን ኢትዮጵያ አድባራት ተጠብቆ መቆየቱ በቤተክርስቲያን ድርሳናት በዝርዝር ሰፍሯል።
እኛ ደግሞ ታቦቱ በቴክኖሎጂ ወይም በቁፋሮ የሚገኝ ተራ ዕቃ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጥና የሚሰወር መንፈሳዊ ኃይል እንደሆነ እናምናለን።
ይህ ዘገባ የኢትዮጵያን ሚና እና ታሪካዊ ባለቤትነት ሆን ብሎ ችላ ማለቱ፣ ምናልባትም በታሪክ ምርምር ስም የሚደረግ የፖለቲካ ጨዋታ አካል ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አድሮብኛል። ታቦቱ በአካል አክሱም ውስጥ ቢገኝም፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኃይሎች ግን የራሳቸውን ትርክት (Narrative) ለመፍጠር እየተሯሯጡ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶችም አሉት።
እናንተስ ምን ትላላችሁ?
የዓለም ሳይንቲስቶችና የታሪክ ጸሐፊዎች ታቦቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ነው እያሉ የሚሰጡት መግለጫ በእኛ ታሪክና እምነት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል ?
Source: GetuTemesgen









No comments yet.