- Advertisement -
Sidebar AD

አሰቃቂ ግድያ በማድረስ በከባድ ውንብድና ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጣ

ተከሳሽ ማሙሽ ማርቆስ በ1997 ዓ/ም የወጣውን የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ አንቀጽ 671 ንዑስ አንቀጽ (2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላፍ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጣ።

ተከሳሽ ማሙሽ ማርቆስ ሳልቄ ካልተያዘ ግብረ-አበሩ ጋር በመሆን ያልተገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት በማሰብ፣ የካቲት 22 ቀን 2018 ዓ.ም (በግምት ከምሽቱ 1:30 ሰዓት) በአርባ ምንጭ ከተማ፣ ሼቻ ክፍለ ከተማ፣ ቤሬ ዕድገት በር ቀበሌ ልዩ ስሙ “ሙሉ ወንጌል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የፅድቅ ቃል አለምአቀፍ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ አጥር ዘሎ በመግባት ውንብድና ወንጀል ፈጽሟል።

ተከሳሹ ፣ ሟች ነህምያ ተስፋዬ የተባለችው ወጣት በስልክ እያወራች በነበረችበት ወቅት፣ የዋጋ ግምቱ 17,000 ብር የሚያወጣ የ”Infinix” (ኢንፊኒክስ) ስልክ በሃይል ለመንጠቅ ሞክሯል። ሟች ንብረቷን ለማስጠበቅ ስትታገል፣ ተከሳሹ በያዘው ስለታማ ቢላዋ በሰውነቷ ላይ አራት የተለያዩ ቦታዎች (ደረቷ እና እጆቿ ላይ) ደጋግሞ በመውጋት ከባድ ጉዳት አድርሶባታል። ሟች በደረሰባት ከፍተኛ ደም መፍሰስ ምክንያት ወደ አርባ ምንጭ ሆስፒታል ተወስዳ በህክምና ሲረዳት የቆየች ቢሆንም፣ በዚያው እለት ሌሊት 6:00 ሰዓት አካባቢ ህይወቷ አልፏል።

በሂደቱ ላይ ዐቃቤ ህግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ በበቂ ሁኔታ አስረድቷል።

ተከሳሹ መጀመሪያ “እከላከላለሁ” በማለት ቀጠሮ ቢወስድም፣ በቀነ ቀጠሮ ዕለት ግን “የሚያቀርበው የመከላከያ ማስረጃ የለኝም፤ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ፍርድ እቀበላለሁ ” በማለት ቃሉን በችሎት ሰጥቷል።

የተከሳሹን የክስ መዝገብ ሲመለከት የቆየዉ የአርባምንጭ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የነፍስ ግድያ ወንጀል ክስ የቀረበለትን ተገቢ የሆነ ማስረጃ መሠረት በማድረግ ሚያዝያ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሽ ማሙሽ ማርቆስ የተባለውን ተከሳሽ በዕድሜ ልክ በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

አርባምንጭ ከተማ መ/ኮሚዩኒኬሽን


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1