#Ethiopia | መክሊት ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ ”25 ዓመታት ህልሞችን ያሳካ – ብሩህ ነገን የሚያፈካ” በሚል መሪ ቃል የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን በነገ ዕለት በአዲስ አበባ በደመቀ ሁኔታ እንደሚያከብር አስታወቀ።
ተቋሙ ባለፉት 25 ዓመታት የባንክ አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በመድረስ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጿል።
የመክሊት ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘገየ ባንቴ በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ ተቋሙ ላለፉት 25 ዓመታት ትኩረቱን የሀገሪቱ ግማሽ አካል በሆኑት ሴቶች እና ከጠቅላላው ሕዝብ 70 በመቶውን በሚይዙት ወጣቶች ላይ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል።
ባንኮች የሚጠይቁት የንብረት ዋስትና የሌላቸውን እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች የብድርና የቁጠባ ተጠቃሚ በማድረግ፣ የገንዘብ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ስልጠናዎችንና ሙያዊ ድጋፎችን ሲሰጥ መቆየቱን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ከ93 ሺህ በላይ የብድርና የቁጠባ ደንበኞች ያሉት ሲሆን በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስፋት እየሰራ ይገኛል።
የ2030 ስትራቴጂክ ዕቅድ በመቅረጽ፣ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 60 ለማድረስ እና አገልግሎቱን ወደ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ለማስፋፋት እየሰራ ነው።
የተቋሙ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታምራት ጥሩ ነህ በበኩላቸው፣ መክሊት ያለ ንብረት ዋስትና (በቡድን ዋስትና) ብድር በመስጠት የዜጎችን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ፣ በአሁኑ ወቅት አትራፊና ጠንካራ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ባለፈው ዓመት አስቸጋሪ በነበረው የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ እንኳን 54 በመቶ የአክሲዮን ትርፍ ማስመዝገቡን የገለጹት ሰብሳቢው፣ በቀጣይም ተቋሙ ወደ ካፒታል ገበያ ለመግባት የምዝገባ ሂደት ላይ መሆኑን አብስረዋል። ይህም ተቋሙ ይበልጥ አቅሙን አሳድጎ ለደንበኞቹ ሰፊ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያቀርብ ያስችለዋል።
ተቋሙ በዛሬው ዕለትም በአዳማ ከተማ ያስገነባውን ለንግድ እና ለራሱ አገልግሎት የሚውል ባለ አምስት ወለል አስገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገ ሲሆን በህንጻው ላይ በተከፈተው ቅርንጫፍ ላለፉት ዓመታት ተቋሙን በትጋት ባገለገሉት ወ/ሮ ነጻነት መንግስቱ ስም ሰይሟል።
38 ቅርንጫፎች ያሉት የመክሊት ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ አጠቃላይ ካፒታሉ 577,000,000 ብር ሲሆን ጠቅላላ ሃብቱ 1.5 ቢሊዮን ተቀማጭ ገንዘቡ ደግሞ 592 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
ተቋሙ በ2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ወር ባለው ጊዜ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ያተረፈ ሲሆን ሆኖም በባለድርሻዎቹ ይሁንታ የትር ክፍፍል ሳይደረግ የካፒታል እድገት ተደርጓል።
መክሊት ማይክሮ ፋይናንስ “ዋና ዓላማችን ብድር መስጠት ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድል መፍጠር ነው” በሚለው መርሁ፣ ከመንግሥት አካላትና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎች ጋር በቅንጅት መስራቱን እንደሚቀጥል በመግለጫው ተመላክቷል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu



Source: GetuTemesgen









No comments yet.