#Fastmereja: በኢትዮጵያ የካንሰር ሕክምና ተደራሽነትን ለማስፋትና ታካሚዎች ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱበትን እንግልት ለማስቀረት ያለመው ”ክብር ደስታ የካንሰር ማዕከል” በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ ተመረቀ፡፡
ማዕከሉ ”ክብር” እና “ደስታ” የሚሉትን እሴቶች በመያዝ፣ ታካሚዎችን በሰብአዊ ክብርና በደስታ ማገልገልን ዓላማ ያደረገ ሲሆን፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከርኅራኄ ጋር በማጣመር አዲስ የሕክምና ምዕራፍ እንደሚከፍት ይጠበቃል።
የማዕከሉ አንዱ ትልቅ ስኬት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው የተሟላ የጡት ካንሰር ምርመራና ሕክምና መስጠት የሚችል ተቋም መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ እንደ 3D ማሞግራፊ (3D Mammography)፣ ስቴሪዮታክቲክባዮፕሲ (Stereotactic Biopsy) እና የጡት ኤም.አር.አይ (Breast MRI) ያሉ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን አሟልቷል፡፡
ማዕከሉ መጀመሪያ ትኩረቱን በጡት ካንሰር ላይ ቢያደርግም፣ በአሁኑ ወቅት ሌሎች የካንሰር ዓይነቶችንም ማከም መጀመሩ ተገልፆ በዘርፉ የሰለጠኑ የኦንኮሎጂ ስፔሻሊስቶች፣ ጠቅላላ ሐኪሞች እና የኦንኮሎጂ ነርሶች በቡድን በመሆን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ ሕክምና ለታካሚዎች ይሰጣሉ ተብሏል።
ክብር ደስታ የካንሰር ማዕከል በረዳት ሜዲካል ፕላዛ (Redat Medical Plaza) ውስጥ ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ መገኘቱ ታካሚዎች ከአንድ ጣራ ሥር ሁሉንም አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችላቸዉ ሲሆን ይህም የተቀናጀ የካንሰር ቀዶ ጥገና፣ የኑክሌርሜዲስን፣ የላቦራቶሪ እና የድንገተኛ አደጋ ሕክምናን ያጠቃልላል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ ካንሰር በጊዜ ከተደረሰበት መዳን የሚችል ሲሆን ማዕከሉ ታካሚዎች ከበሽታው አገግመው የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችል (CANCERVIVE/CANTHRIVE) የስነ-ልቦና እና የህክምና ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቱንም አስታውቋል።
በምረቃው ወቅት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘዉዴን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የዘርፉ ተዋናዮች የተገኙ ሲሆን፤ ይህ ማዕከል መከፈቱ በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ያለውን ክፍተት ከመሙላቱም በላይ፣ ዜጎች በሀገራቸው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።



Source: FastMereja








No comments yet.