የዱባ ወጥ በተለይ በጾም ወቅት በጣም ተመራጭ፣ ቀለል ያለና ጣፋጭ ምግብ ነው። አዘገጃጀቱም አጭር ጊዜ የሚወስድና ቀላል ነው።

- Advertisement -
Sidebar AD

ባለሙያዎች እንደሚመክሩት የዱባ ወጥን በሁለት መንገድ (በቀይ ወይም በአልጫ) መስራት ይቻላል። እዚህ ጋር የቀይ ወጥ አዘገጃጀቱን እንመልከት፡-

የሚያስፈልጉ ግብዓቶች
📌ዱባ፡ 1 መካከለኛ (ተልጦና ተቆራርጦ የታጠበ)
📌 ሽንኩርት፡ 2 መካከለኛ (ደቅቆ የተከተፈ)
📌 በርበሬ፡ እንደ ፍላጎትዎ (ብዙውን ጊዜ 1-2 የሾርባ ማንኪያ)
📌 ዘይት፡ ግማሽ ሲኒ
📌 ነጭ ሽንኩርትና ዝንጅብል፡ የተፈጨ
📌 ጨው፡ እንደ አስፈላጊነቱ
📌 ቅመማ ቅመም፡ (ኮረሪማ ወይም መከለሻ ቅመም)

የዝግጅት ቅደም ተከተል
1. ሽንኩርቱን ማቁላላት፦ በመጀመሪያ ሽንኩርቱን በድስት ውስጥ አድርገው ውሃው እስኪመጥ ድረስ በደንብ ያቁላሉት። ከዚያም ዘይት ጨምረው ሽንኩርቱ መልክ እስኪያወጣ ድረስ ማቁላላቱን ይቀጥሉ።

2. በርበሬ መጨመር፦ በርበሬውን ጨምረው ከሽንኩርቱ ጋር በደንብ እንዲዋሃድ ያድርጉ። በርበሬው እንዳይቃጠል ጥቂት ውሃ ጠብ እያደረጉ ለ10 ደቂቃ ያህል ማቁላላት ጥሩ ጣዕም ይሰጠዋል።

3. ነጭ ሽንኩርትና ዝንጅብል፦ የተፈጨውን ነጭ ሽንኩርትና ዝንጅብል ጨምረው ለጥቂት ደቂቃዎች አብረው ያቁላሉት።

4. ዱባውን መጨመር፦ የተቆራረጠውን ዱባ ድስቱ ውስጥ ይጨምሩት። ዱባው ውሃ የማውጣት ባህሪ ስላለው መጀመሪያ ላይ ውሃ ሳይጨምሩ ከቁላላው ጋር በማዋሃድ ለጥቂት ደቂቃዎች በክዳን አፍነው ያብስሉት።

5. ውሃ መጨመር፦ ዱባውና ቁላላው ከተዋሃዱ በኋላ፣ ዱባው እስኪበስል ድረስ የሚበቃውን ያህል ጥቂት የፈላ ውሃ ይጨምሩበት። (ዱባ ቶሎ ስለሚበስል ውሃ እንዳያበዙ ጥንቃቄ ያድርጉ)።

6. ማጣፈጫ፦ ዱባው በስሎ ሲጨርስ ጨውና የሚፈልጉትን የቅመም አይነት (ኮረሪማ ወይም መከለሻ) ይጨምሩበት።

7. ማውጣት፦ ወጡ ዘይት ሲያወጣና ዱባው በደንብ ሲበስል (አንዳንዶች ዱባው እንዲፈራርስ ይፈልጋሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ሳይፈራርስ ይመርጣሉ) ከእሳት ላይ ያውርዱት።

ተጨማሪ መረጃ፦
• ለአልጫ ወጥ፦ በርበሬውን በመተው በምትኩ እርድ በመጠቀምና ቃሪያ በመጨመር ከላይ በተጠቀሰው መንገድ መስራት ይቻላል።
• ለየት ያለ ጣዕም፦ ወጡ ሊወጣ ሲል ጥቂት የጥቁር አዝሙድ ዱቄት ቢጨመርበት ልዩ መዓዛ ይሰጠዋል።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: