የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷ እና ምልጃዋ አይለየን !!!

- Advertisement -
Sidebar AD

በእውነት ወላዲተ አምላክ ትባላለች

ቅዱሳን የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር እንዴት እንደሚገልጹት ተጨንቀው በምን በምን እንመስልሻለን በማለት ምሳሌ ማጣታቸውን ተናግረዋል። በቤተክርስቲያናችን ዘወትር የሚነሱት ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም፤ የብህንሳው አባ ሕርያቆስና ኢትዮጵያዊው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይገኙበታል። የእመቤታችንን ክብር ያለተረዱ ሰዎች ለምን እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንደምናመሰግናት ዘወትር በጸሎታችን እንደምናነሳት ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ። የተዋሕዶ ልጅ ሁሉ ከሕጻንነቱ ጀምሮ የእመቤታችንን ምስጋና ይማራል፤ ኣባታችን ሆይ ብሎ ጸሎት የጀመረ በመልኩ ቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን ብሎ ድንግል ማርያምን ያመሰግናል። ቤተክርስቲያናችን ድንግል ማርያምን ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ በማለት ክብሯን ትገልጻለች። ድንግል ማርያምን ልዩ የሚያደርጋትና የክብሯ መገለጫ ከሆኑት የሚከተሉት ይገኙበታል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት። አንዳንዶች የአምላክ እናት የሚለውን አጠራር መቀበል አይፈልጉምና የኢየሱስ እናት ማለትን ብቻ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ አጠራር በበጎ ህሊና ካየነው ችግር ባይኖርበትም ወላዲተ አምላክ ብሎ መጥራት የበለጠ የተዋሕዶን ምሥጢር ይገልጣል፡፡ መናፍቃን የኢየሱስ እናት ብለው ሲጠሩ ያሳደገም እናት ተብሎ ሊጠራ ይችላልና በሚል ስሜት ነው። ቀድሞም ንስጥሮስ የተባለው ከሃዲ በ431 ዓ.ም እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባም ብሎ በክህደት በመነሳቱ በኤፌሶን ጉባኤ ውግዘት እንዲተላለፍበት ሆኗል። እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ናት የሚለው አነጋገር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑን ይገልጻል። በሐዋርያት ሥራ 2÷25—32 ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ ዳዊትን ጠቅሶ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነትና ከስጋ ጋር መዋሐድ በሰፊው ያትታል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ሥጋዬ ብሎ የተናገረው በእርግጥም የእርሱ ሥጋ ነው ነገር ግን ሥጋዬ አይበሰብስም ብሎ ሲናገር ደግሞ ምሥጢራዊ ትርጉም እንዳለው ያመለክታል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ሲነሳ ብቻ ነውና። ወንጌላዊያኑ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ሉቃስ የጌታችን የልደት አቆጣጠር ብለው ያስቀመጡት ጌታችን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተዋሐደውን ሥጋ መሠረት አድርገው ነውና፤ ይህ ባይሆን ኖሮ የትውልድ ሐረግ ለመቁጠር ባልተነሱ ነበር። ስለዚህ እኛ ኦርቶዶክሳውያን እናታችንን ወላዲተ አምላክ ብለን ስንጠራት የተዋሕዶን ምሥጢር እንመሰክራለን። ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊት ድንግል ናት፡፡ ቅዱስ ኢሳይያስ በትንቢቱ 7÷14 “ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች” ብሎ ጽፏል፡፡

ይህን ብሎ በመጻፉም ነቢዩ ኢሳይያስ በመጋዝ ተሰንጥቋል፡፡ ለዚያም ነው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን 11÷37 ቅዱሳን ነቢያት ስለ ክርስቶስ ትንቢት መናገርን ብቻ ሳይሆን በዚሁ ትንቢትም ምክንያት ሕይወታቸውን መስጠታቸውን የሚነግረን። ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር የአካሉ ማደሪያ መሆኗን የሚነግረን አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም በዚህ ታላቅ ምሥጢር እጅግ ተደንቆ “ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፤ ሳይወሰን ፀነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማኀፀንሽ ተወሰነ፤ መመጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ” በማለት እመቤታችን የወልድ ማደሪያ መሆኗን መስክሯል። ስለዚህ ነው ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ የምንላት አምላክ በማኀፀንዋ 9 ወር ከ 5 ቀን ተቀምጦ በድንግልና ወልዳዋለችና። ገዳማውያንም እንደ ቅዱሳኑ ያመሰግኗታል በምልጃዋም ታረጋጋቸዋለች፡፡ ገዳማቸውን እንደግፍ በዓታቸውን እናጽና፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: