በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው 1ኛ ተከሳሽ አቶ ኑሪ ሁሴን ኢንደሳ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ሲሰሩ፤ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የባንኩ ደንበኛ ከሆኑት የግል ተበዳይ ቱጂ አማን ኩራ ከ1.7 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀብለዋል በሚል ከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የባንኩ ደንበኛ የሆኑት የግል ተበዳይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሙራባሃ ተገለባባጭ ፋይናንስ አገልግሎት ለጥራጥሬ እህል መግዣ የሚውል 184 ሚሊዮን ብር ብድር ይጠይቃሉ።
ብድሩን ለማግኘት ባንኩ ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታ በሙሉ አሟልተው ፋይሉ ለተገቢው ውሳኔ ሲቀርብ ተከሳሽ በባንኩ ውስጥ ያላቸውን ስልጣን በመጠቀም ቀኑና ወሩ በውል ባልታወቀበት በ2016 ዓ/ም ተበዳይን በማግኘት ብድሩ እንዲፈቀድላቸው በገንዘብ እና በአይነት ያልተገባ ጥቅም እንዲሰጡ መጠየቁንና ይህንንም ካላሟሉ ብድሩን እንዳያገኙ እንደሚያደርጓቸው ስለመግለጻቸው በክስ መዝገቡ ተመላክቷል።
የግል ተበዳይ አቶ ቱጂ አማን ኩራ ተከሳሽ የተጠየቁትን ገንዘብ ገቢ የሚያደርጉበትን የባንክ ሂሳብ ቁጥር በመስጠት እንዲሁም በአይነት የጠየቀውን ንብረት የሚያቀርቡበትን ቦታ በአካል ካሳዩ በኋላ ተበዳይ የጠየቁት ብድር ይፈቀድላቸዋል።
አቶ ቱጂ አማን የጠየቀውን ያልተገባ ጥቅም ካልሰጠሁ ተከሳሽ ይጎዳኛል ብለው በመፍራት ተበዳይ አንድ ሚሊዮን ብር ወደ 1ኛ ተከሳሽ ባለቤት እህት 2ኛ ተከሳሽ ሪሀና ወርቅነህ ዋቆ ድርጅት (አና ትራቭል ኤጀንት) የባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዲገባለት ያደረገ በመሆኑ፤ እንዲሁም የ1ኛ ተከሳሽ ባለቤት በሆነችው ወ/ሮ ሀቢባ ወርቅነህ ዋቆ ስም ተመዝግቦ በመገንባት ላይ ለሚገኘው ህንጻ ግንባታ የሚውል ጠቅላላ ዋጋው 740 ሺህ ብር የሆነ 400 ኩንታል ሲሚንቶ ህንጻው በሚገነባበት ቦታ ድረስ እንዲራገፍለት ያደረገ መሆኑን የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል።
በሌላ በኩል 3ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሪሀና ወርቅነህ ዋቆ ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው ገንዘቡን ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወንጀል የፈፀመውን ግለሰብ ከህግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ በማሰብ 600 ሺህ ብር ወደ 1ኛ ተከሳሽ ሂሳብ ቁጥር እንዲተላለፍ በማድረግ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ተጠርጥረውክስ ተመስርቶባቸዋል።
ክሱ የቀረበለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ከተከሳሽ የክስ መቃወሚያን በፅሁፍ ለመቀበል ለግንቦት 3 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።









No comments yet.