ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጤና ተቋማት ለታማሚ አይሆኑም” ሲሉ ተናገሩየኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐ…

- Advertisement -
Sidebar AD
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጤና ተቋማት ለታማሚ አይሆኑም” ሲሉ ተናገሩ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም የጤና ተቋም ለበሽተኛ ወይም ለታማሚ የሚሆን አይደለም” ሲሉ የማህበራዊ ልማት እመርታ ግንባታ በሚል ርዕስ  በተዘጋጀ መድረክ ላይ ገለጹ፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ በህክምናው ዘርፍ ላይ ሙያ ብቻ በቂ አይደለም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የህክምና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ለታማሚ አይሆኑም፤ ምክንያቱ ደግሞ በሽተኛ ነጭናጫ ነው” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋማቱ አለ ያሉት ሽታም ምቹ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንን ለማስተካከል ደግሞ ስራዎች እንደሚስፈልጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በዚህ መሠረትም ችግሩን ለመቀነስ ሆስፒታሎችንና ጤና ጣቢያዎችን ለማሻሻል እና ለማደስ  እየተሞከረ ነው ያሉት ዐቢይ መንግስታቸው ይህን ተከትሎ ሊያስገነባው እንቅስቃሴ ስለጀመረለት ሆስፒታል አብራርተዋል፡፡
“በጫካ ፕሮጀክት ላይ ከሙዚየም ግንባታ ቀጥሎ በዓለምአቀፍ ደረጃ ትልቅ ሆስፒታል በመስራት ወደ ውጭ የሚወጡ ታማሚዎችን እናስቀር ብለን በማሰብ የሆስፒታሉ ዲዛይን ተሰርቶ ጨረታ ሲወጣ ለህንጻው ግንባታ ብቻ 300 ሚሊዮን ዶላር ተጠይቀናል” ሲሉም በመድረኩ ገልጸዋል ።
“ለግንባታው ይሄን ያህል ከተጠየቅን ለሆስፒታሉ እቃዎች ግዢ ደግሞ የሚወጣው ወጪ ቀላል አይደለም” በማለት የሚጠይቀውን የገንዘብ መጠን ከፍተኛነት ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ   “ሆስፒታሉ ቢገነባ ሰዎች ውጪ ሄደው ከመታከም ይድናሉ ነገር ግን ኢንቨስትመንቱ ቀላል አይደለም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘው “አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ 20 በሚጠጉ የግል ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያዎች ላይ ያየሁትን ነገር ለማስተካከል እና እዛው እየፈቱ ለመሄድ እሞክራለሁ፤ ነገር ግን እጄ ሊሞላ አልቻለም፤ የአቅም ውስንነት ገጥሞናል” ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሀኪሞች ቦታ እና ሆስፒታል ኖሯቸው ከሚሰደዱ እና ከሀገር ከሚወጡ ሀገራቸው ላይ እንዲሰሩ እፈልጋለሁ ሲሉም ተደምጠዋል።
“ጤና እና ሰላም ካልጎደለ አይታወቅም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ሁለት ነገሮች የጎደሉባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው የሚያውቁት  እና የሚረዱት በማለት በአጠቃላይ ችግሩን ለመፍታት የመንግስታቸውም ፍላጎት መሆኑን አጽዕኖት ሰጥተውበታል።
የሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ እና የጽዳት ሁኔታውን ማየት የሀኪሞች ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው ዋጋ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡  ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያይዞም በርካታ ስራዎችን እየሠሩ መሆኑን የገለጹት ዐቢይ በተለይ ከመሠረተ ልማት ጋር በተገናኘ አካታች ተደርጎ እየተሠራ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡
“የአጥንት መገጣጠሚያ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም  እቃዎች በመንግስት በጀት የተገኙ ሳይሆኑ   ለምነን ነው ያመጣነው” ብለዋል፡፡
“አብዛኛው ነገር  በልመና ነው የሚሰራው” የሚለውን ትኩረት ሰጥተው ያብራሩት “ሥራ የላቸውም ወይ? እንዴት ለምነው የቱሪዝም መዳረሻ ይሰራሉ? የሚሉ አሉ፤ ይህ ግን ኢትዮጵያ ያለችበትን የችግር አረንቋ የማይረዱ፣ ማኪያቶ ቢያምራቸው መጠጣት የሚችሉ እና ዓለም ሁሉ እንደዛ የሚመስላቸው  ሰዎች ናቸው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
በመንግስታቸው በጀት ብቻ ሳይሆን ለምነው ቢሰሩም የሀገሪቱ ሁኔታ ግን ገና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
@seledadotio
@seledadotio

Source: SeledaPost

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2