#Ethiopia | የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የ2017 በጀት ዓመት ሙሉ ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀምን ይፋ አድርጓል፡፡
ግሩፑ ባወጣው መረጃ መሠረት በኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች አማካኝነት በ2017 የምርት ዘመን 32,806.25 ቶን ስኳር እና 46,204.86 ቶን ሞላሰስ ማምረት ተችሏል፡፡
ይህ አፈፃፀም ከቀደመው የ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በስኳር ምርት የ33 በመቶ እንዲሁም በሞላሰስ ምርት የ46 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
በፋይናንስ ረገድ ሁለቱም ፋብሪካዎች በ2017 በጀት ዓመት ከወጪ ቀሪ የ1.5 ቢሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ትርፍ ያስመዘገቡ ሲሆን በወቅቱ ያልተሸጡ ምርቶችን ጨምሮ አጠቃላይ ትርፋቸው 3.159 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡
ፋብሪካዎቹ ባሳዩት ውጤታማነት ምክንያት ለሠራተኞቻቸው የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ለመንግስት የሚከፈል የታክስ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ196 በመቶ በመጨመር 970.4 ሚሊዮን ብር ለሀገር ገቢ ሆኗል፡፡
ለስኳር ኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ (SIDF) ደግሞ 686.1 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ ተደርጓል፡፡
የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀምን በተመለከተ በሁለቱ ፋብሪካዎች 28,741 ቶን ስኳር እና 24,694 ቶን ሞላሰስ ተመርቷል፡፡
ምንም እንኳን በአካባቢው በነበረው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የምርት ሂደቱ ለጊዜው ቢቆምም በደረቅ ወራት በሚከናወነው ሁለተኛ ዙር ምርት የዓመቱ አፈፃፀም ከ2017 የተሻለ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 374.7 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ የተመዘገበ ሲሆን ለመንግስት 838.7 ሚሊዮን ብር ታክስ ተከፍሏል፡፡
ከስኳር ምርት ባሻገር ፋብሪካዎቹ በግብርና እና በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ተሰማርተው የገቢ ምንጫቸውን በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡
በኦሞ እና በአርጆ ዴዴሳ ፋብሪካዎች የዶሮ፣ የዓሳ፣ የከብት ማድለብ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመከናወኑ ተጨማሪ 30.69 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡
በአጠቃላይ ከለውጡ በፊት በከፍተኛ ዕዳ እና የአሠራር ችግር ውስጥ የነበሩት እነዚህ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት ውጤታማ ወደመሆን ተሸጋግረዋል፡፡
ተከማችቶ የነበረውን የቆየ ዕዳ በመክፈል ረገድም በ2017 ዓ.ም 378 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በ2018 ዘጠኝ ወራት ውስጥ 458.8 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈል መቻሉን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በላከልን ሪፖርት አስታውቋል፡፡
#SugarIndustry #EthiopianEconomy #OmoKuraz #Development #Manufacturing #Agriculture #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa


Source: GetuTemesgen









No comments yet.