‘ንቃተ ህሊና’ ዳግም መነጋገሪያ ሆነ፤ በመጨረሻው ቪዲዮ ብዙሃኑን አስለቅሷል፤ ራሱም አልቅሷል

- Advertisement -
Sidebar AD

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ተነስቶ ቲክቶክ ላይ ከወጣባት ቀን ጀምሮ ብዙሃኑን አነጋግሯል። አዲስአበባ ከከተመ በኋላ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቲክቶክ ተጠቃሚን ትኩረት አግኝቷል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ድብልቅ ማርሻል አርት ውድድር እንዲካሄድ፣ በፈር ቀዳጅነት ለመወዳደር ራሱን ካጨበት ቀን ጀምሮም በራስ መተማመኑና በጂም የሚታየው ያልተቋረጠ ትግልና የላብ ጠብታ ብዙሃኑን አስገርሞም ያውቃል።

ሁልጊዜም ‘ታሸፋለህ?’ አልያም ‘የምታሸንፍ ይመስልሃል?’ ተብሎ ሲጠየቅ በልበ ሙሉነት የማሸንፍ አይመስለኝም ግን እንደማሸንፍ አውቃለሁ ይላል። በልቡ አንዳች ጥርጣሬ እንደሌለው ለማሳየት።

ተጋጣሚው ዮሐንስ ሲለሺ (ጆኒ)፣ ከውድድሩ አስቀድሞ በውድድሩ ምን እንደሚገጥመው ያውቃል ነገርግን ለስፖርቱ ጅማሮ ራሱን ሊሰዋ መጥቷል ያለው ከዚያም ከውድድሩ በኋላ ውጤቱ ምንም ይሁን ታሪክ ሥምህን በመዝገቡ ላይ አስፍሯል ሲል ያሞካሸው ወጣት፣ በሚታየው ፍልሚያ ቢሸነፍም ብዙ የማይታዩ የህይወት ትግሎችን ማሸነፉን ትናንት ማታ ለሚሊዮኖች አሳይቷል።

አባቱን በቀኙ፣ እናቱን ከግራው አስቀምጦ እንዲህ አለ፣ ወዳጆቼ፤ እስከዚህም አብራችሁን ስለሆናችሁ አመሰግናለሁ፤ ውድድሩን በደንብ ተወዳድሬ እንደማንኛውም ሰው ባሸንፍ ደስ ይለኝ ነበር። ይህንን ሲናገር ፍጹም ኩራት ከፊቱ ይታያል።

‘አባቴን መሆን አልፈልግም። አባቴ ድሃ ነው። በብዙ ችግር አድጌያለሁ። ትልቁ ህልሜ ለእነሱ መድረስና ልጆቼ እኔ የኖርኩትን እንዳይኖሩ ማድረግ ነው’ ሲል ከውድድሩ ቀደም ብሎ በአንድ ፖድካስት የተናገረው ዮሐንስ ምስክር አበበ (ንቃተ) አቶ ምስክር አበበ በስስት እያዩት ነበር የማታውን ንግግር ያደረገው።

በዚሁ ንግግሩ ቀጠለና፣ በመድረክ ላይ ወጥቼ ደረቴን ነፍቼ ስናገር፣ መንገድ ላይ ደረቴን ነፍቼ ስራመድና የምደርስበት አለ ስላችሁ የተነሳሱበትን ስለማውቅና የምደርስበትን አእምሮዬ ስለሚያሳየኝ ነው ሲል ተናግሯል።

በዚህ መካከል የአባቱን የለቅሶ ድምፅ ሰምቶ ‘አታልቅስ አባቴ’ ሲል የተናገራት ቃል በአሁኑ ሰዓት በማህበራዊ ሚዲያ በእጅጉ ከተወደዱና ብዙሃን ከተጋሯቸው ቃላት አንዷ ሆናለች።

እናቱ እቴነሽ ባዩ ከጎኑ ተቀምጣ ውድድሩ ብዙሃንን አስተዋውቆኛል፤ ሳንቲም ሰብስቤያለሁ ለእናቴም ቤት እገነባለሁ ያለው ንቃተ ህሊና ለእናቴ ስልም ምንም ነገር አደርጋለሁ ብሏል። ይህንን ከመናገሩ በፊት ከጭቃ የተሰራች ደሳሳ የቆርቆሮ ክዳን ቤታቸውን፤ ከውስጥ በሸራ የተለጠፈችን ደሳሳ ጎጆ እያሳየ ነበር።

ይህ ቪዲዮ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ከሰፈረባት ሰዓት ጀምሮ እጅግ በጣም ብዙ ታዋቂ ሰዎች በዚያ ሥር ያላቸውን ክብርና ፍቅር ገልጽውለታል። ለተናገሩትም ቃል ይቅርታ ጠይቀውታል።

በተጨማሪም የህይወት መንገዱ ለብዙ ወጣቶች አበረታች እና አነቃቂ እንደሆነ ጠቅሰው ‘አሸንፌያለሁ የምለው ለዚህ ነው’ ያለውን ንቃተ ህሊና ‘እውነትም አሸንፈሃል’ ብለውታል። እሱም ኮሜንት ሳነብ አለቀስኩ ሲል መልሷል።

የዚህ ወጣት ህይወት የጀመረው ቲክቶክ ላይ አይደለም። ሰፈር ከማስቸገር፣ ከመደብደብ፣ ከመንጠቅና ወደ አዲስአበባ ጎዳናዎች ከመሰደድና ከመኖር እንጂ።

በአዲስአበባ በጎዳና የኖረው፣ በልጅነት ጉልበቱ ሳይፀና የቀን ሥራ ሰርቶ፣ ባሬላ ተሸክሞ የህይወት መንገዱን ለማቅናት በቆጠባት ሳንቲም ወደ ወላጆቹ ተመልሶ ጠንክሮም ተምሮ፣ ጎበዝ ተማሪ ሆኖ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ከዚያም ወጥቶ ህይወትን ተጋፍጦ አሸናፊነቱን ያወጀ ወጣት ነው።

ህይወት ስለማሸነፍ አይደለችም። “ምን ያህል ትቀጠቅጣለህ ሳይሆን ተቀጥቅጠህ ምን ያህል ወደ ፊት መራመድ ትችላለህ’ ነው ሲል የሚናገረው ንቃተ ህሊና በህይወትም በተፋላሚውም ተቀጥቅጦ፤ ራሱን ለስፖርቱ፣ ራሱን ለእናት አባቱ ሲል ሰውቶ ሳይቆም፣ የብዙሃኑን ልብ ዳግም አሸንፎ የቀጠለ የዚህ ዘመን ትውልድ ተምሳሌታዊ የአይበገሬነት ተምሳሌት ወጣት ሆኗል።

Via: ዶች ኤችዲ






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1