ገበታ ለሀገር ! ገበታ ለጣና!

- Advertisement -
Sidebar AD

ባህርዳር የግዙፉን የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት የምረቃ ስነስርአት እያስተናገደች ነው!
______________________________

ዛሬ ሚያዝያ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በውቧ ባህር ዳር ከተማ የግዙፉ የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት መመረቅ ተበስሯል።

በደቡባዊ የጣና ሐይቅ ዳርቻ፤ በባህር ዳር ከተማ የተገነባው የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ለጣና የቀረበ የጎርጎራን ብርሃን በሌላኛው ዳርቻ ያስቀጠለ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ነው።

ይህ ውጥን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የጎርጎራን ታላቅ ስራ ሙሉ ለማድረግ በሌላኛው የጣና አቅጣጫ፥ በውቧ ባህር ዳር የሚተሳሰሩ ሁለት የአንድ ሐይቅ ዳርቻ ገናና ህልሞችን ለማሳካት በገበታ ለሃገር ያለሙት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ቀደምቷን የዐፄ ሱስኒዮስ መናገሻ ጎርጎራን ከዘመናት ጨለማ በኋላ ታላቅ ብርሃን እንድትጎናፀፍ ያደረጉበትን እጅግ ድንቅ አሻራ ተከትሎ ዳግም በዐፄ ሱስኒዮስ ልጅ በፋሲለደስ መናገሻ ጎንደር አዲስ ነገር አሳዩ።

በመከራ ውስጥ የኖረውን የጎንደር አብያተ መንግሥታት ግብረ ሕንፃ እንደ አዲስ ነፍስ የዘራበትን የቅርስ ጥገና እና ልማት ዕውን አደረጉ። ይህ የቅርስ ጥገናና ልማት የዓለም ቅርሱን ታሪክ ወደ ላቀ ስኬት ያሻገረ የዘላቂ ቱሪዝም ትልቅ አቅም ነው።

የቀጠናውን መፃኢ ዕድል ነገውን ያስናፍቃል ያስባለው ሌላው ፕሮጀክት በጎንደር ከተማ የሚገኘው የመገጭ የመጠጥ፣ የመስኖ እና ሁለንተናዊ ልማት አቅም የሆነው ግድብ ነው። ግድቡ የውሃ እጥረት ላለባት ጎንደር ከቱሪዝም ልማት አኳያ ለውሃ ቱሪዝምና መዝናኛ ኢንቨስትመንት አዲስ ዕድል ይዞ እየመጣ ነው።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በገበታ ለሀገር እንደለማው ሁሉ ይህ ራዕይ እንዲዘልቅና እንዲስፋፋ ገበታ ለሀገር በግል ኢንቨስትመንትም እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት የመሪነት ሚና ሀሳባቸውን በመግዛት የቤአኢካ እና የእህት ኩባንያዎቹ መሥራች አቶ ካሳሁን ምስጋናው ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርትን በገበታ ለሀገር ማዕቀፍ ውስጥ 4.5 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርገው በሁለት አመት ከስድስት ወር ግዜ ውስጥ እውን አድርገዋል።

ከዚህ ሪዞርት እና ከሌሎች ገናና ውጥኖች ዕውን መሆን ጀርባ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ረገድ ከሀገር ልማት ጎን የቆመው የቤአኢካ ንግድና ኢንቨስትመንት ሚና የላቀ ነው።

በተለይም የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሀገር ወዳዱ አቶ ካሳሁን ምስጋናው በጎርጎራ ኢኮ ቱሪዝም ግንባታ በኮንትራክተርነት በታሰበው ጊዜ፣ በታለመው ጥራት እና በሚያኮራ ኃላፊነትን የመወጣት ስኬት አጠናቀዋል።

በተመሳሳይ እንደ ሀገርም ባልተለመደ ሁኔታ በሀገር ልጅ ብቃት እና ኃላፊነትን የመወጣት ተግባር ምስጋና የቀረበለትን የጎንደር አብያተ መንግሥታት ግብረ ሕንፃ የቅርስ ጥገናና ልማት ስራ ሌላው ስለ ሀገር የተወጡት ኃላፊነት ነው።

በዚሁ ‘በጎንደር እስከ ምፅአት’ በሚል ሲፌዝበት የኖረውን የመገጭ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠ ከባድ የቁጭት አደራ እና ኃላፊነት ተረክበው የግንባታ ሂደቱን በሚያስደንቅ ፍጥነት አሳክተው በመጠናቀቂያው ምዕራፍ ሊገኝ ችሏል።

አሁን ደግሞ በሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ ቦታ የተሰጠው የቱሪዝም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ውጥንን ለፍሬ ያበቁት አቶ ካሳሁን ምስጋናው በሌሎች ኢንቨስትመንቶቻቸው ካሳኩት ልምድ በመነሳት መንግስት ትልቅ ትኩረት የሰጠውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በግሉ ዘርፍ ለማልማት፣ ከመገንባት ልምድና አቅማቸው በተጨማሪ ሮዳ ሆስፒታሊቲ ግሩፕን አቋቁመዋል።

አቶ ካሳሁን እነኚህ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ሆነው ሀገር እና ህዝብ የጣሉባቸውን ኃላፊነቶች እንዲወጡ በማስቻል ረገድ የፌዴራል ፣ የክልል አንዲሁም የከተማ አስተዳደሮች ትልቁን ሚና እንደተጫዎቱ አፅንዎት ሰጥተው ገልጸዋል።

በተለይም የክልሉ መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን የቱሪዝም አብዮት ራዕይ ተቀብሎ ድርጅታቸው እና እሳቸው የተጣለባቸውን አደራ በአግባቡ እንዲወጡ ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይ የማስፋፊያ ስራዎቹ ተጨማሪ አያሌ እቅዶችን የያዘው ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ከጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ጋር በመቀናጀት በሮዳ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ስር ይተዳደራል።

ሮዳ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን እና ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርትን በመያዝ ስራ የጀመረ፤ በቀጣይ ለማስተዳደር በሚረከባቸውም እራሱ በሚገነባቸውም የሆስፒታሊቲ ተቋማት የላቀ፣ ዘመናዊና ተወዳዳሪ አገልግሎትን ለመስጠት ‘ልባችን ኢትዮጵያ ደረጃችን ዓለም አቀፍ!’ በሚል ፍልስፍና ኢንቨስትመንቱን የተቀላቀለ ሀገር በቀል ተቋም ነው።

በገበታ ለሃገር ማእቀፍ ውስጥ በግል ኢንቨትመንት የታነጸው የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ምርቃት ተበስሯል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: