አቡነ ሀብተ ማርያም

- Advertisement -
Sidebar AD

🙏

በነገሥታት ፊት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።

በምጽዋትና በስገድት የምትጋደለው እናቱ ዮስቴና ሀብቷን ሁሉ ለድሆች ሰጥታ ለምናኔ ወደ በረኃ ሄደች። በዚያ ያገኘችው ባሕታዊም በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ከእርሷ ቅዱስ ፍሬ እንደሚወጣ ነግሮ ወደ ዓለም እንድትመለስ አዘዛት። እርሷም “እግዚአብሔር የወደደው ይሁን” ብላ እያመሰገነች ተመልሰች፡፡ የአባቱ የትውልድ ሀገር የራውዕይ በምትባል ሀገር ሲሆን ከዚህች የተባረከች ሴት ጋር ተጋባ። እርሷም በበጎ ምግባርና ሥራ የተጌጠች፣ በሕግ ተወስና በጾም፣ በጸሎት፣ የምትተጋ ነበረች። ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ወንድ ልጅ ወለደች። እንደ ሥርዓቱም ሲጠመቅ የመጽሐፍ ስሙን “ሀብተ ማርያም” አሉት። በሕገ እግዚአብሔር አንጸው አሳደጉት። ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሲወስዱት “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” የሚለውን ጸሎት ቢሰማ እጅጉን ወደዳት። እርሷንም ይዞ ከቤቱ ሌሊቱን የሚጸልይና የሚጋደል ሆነ።

አንድ ቀን የአባቱ በጎቹን ሲጠብቅ የበግ ጠባቂዎቹን “ዛሬ ዝናም ይዘንማልና እንግባ” አላቸው። እነርሱም “ምን ደመና አለ፤ ቀኑ ብራ ነው” አሉት። እርሱ ግን በጎቹን ይዞ ወደ ቤቱ እንደገባ ኃይለኛ፣ ነፋስና መብረቅ የቀላቀለ ዝናም ዘነመ። በሌላም ጊዜ እንዲሁ አንድ እረኛ የሀብተ ማርያምን በትሩን በጉልበት ነጠቀው። “መልስልኝ” ብሎ በስመ እግዚአብሔር ቢያምለውም እምቢ አለው። በተወው ጊዜ እግዚአብሔር ያን እረኛ በአየር ላይ ሠቅሎ አዋለው። እረኞቹም ሀብተ ማርያምን ሲለምኑት፣ እግዚአብሔር ነውና ስለ ስሙ ብሎ የቀጣው መሐሪው እርሱ ከወደደ ይማረው ሲል ያ እረኛ ተፈታና ወረደ። መጥቶም ከአባታችን እግር ስር ወደቀ፡፡ በኋላም ስሟ እለ አድባር ወደምትባል ገዳም ገብቶ ከአባ መልከ ጼዴቅ እጅ መነኰሶ ታላቅ ተጋድሎ ይጋደል ጀመር። በባሕር መካከልም በመቆም መዝሙረ ዳዊትን ይደግምና ግንባሩም የባሕሩን አሸዋ እስኪነካ 500 ጊዜ ይሰግዳል።

እህልም መቅመስን ትቶ የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ። ዐርባ ዐርባ፣ ሰማንያ ሰማንያ ቀንም ያከፍላል። በሌሊትም ቁሞ በማደር በቀንም አራቱን ወንጌላት ዘወትር ይጸልያል። ተጋድሎውንም ያየ አምላካችን ተገለጠለት። አባ ሀብተ ማርያምም ከግርማው የተነሣ ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ። ጌታችንም እፍ ብሉ አጽናንቶ አሥነሳውና ጽኑዕ ተጋድሎው በሰማያት መጻፉን ነገረው፡፡ ስለ ድንግልናው፣ ስለ ምናኔው፣ ስለ ፍጹም ምንኲስናው፣ አራቱን ወንጌላት አዘውትሮ በማንበቡ፣ ረኃብና ጥምን በመታገሡ፣ በልቡ ቂምንና በቀልን ባለማኖሩ፣ ስለ ንጹሕ የክህነት አገልግሎቱና በንጽሕና ስለሚያሣርገው መሥዋዕቱ ሰባት እጅግ የሚያስደንቁ አክሊላትንም አቀዳጀው። የቅዱስ ማቴዎስንና የቅዱስ ማርቆስን ወንጌል ሲያነብ ከሌሎች ሥውራን አበው ጋር የሚገናኝበትን የብርሃን ሠረገላ ሰጠው፡፡

የቅዱስ ሉቃስንና የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል ሲያነብም ሥጋውን ደሙን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድበትን የእሳት ሠረገላ ሰጠውና ቃል ኪዳን ገባለት። መታሰቢያውን ለሚያደርጉና በስሙ ለሚዘክሩ፣ ከእነርሱ ጋር የሚኖርበትን አምስት መቶ የወርቅ አምዶች ያሏትን ቦታ ሰጠሁህ አለው። ቅዱሳን መላእክት ሁሉ እየተደሰቱ አባታችን አቡነ ሐብተ ማርያምን “ወንድማችን ወደማያልቀው ሰማያዊ ደስታ ልንወስድህ መጥተናል” አሉት። ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየው። በኅዳር 26 ቀን ነፍሱ ከሥጋው በሰላም ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በታላቅ ደስታ እያመሰገኑ አሣረጓት። ገዳማውያን የዓለምን ክብር ንቀው ሔደዋልና ጸሎታቸው ኃይልን ታደርጋለች፡፡ በዓታቸውን እናጽና ገዳማቸውን እንደግፍ የበረከታቸው ተሳታፊ እንሁን፡፡

ድጋፍ ለማድረግ፦ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1