መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

- Advertisement -
Sidebar AD

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን!

ብፁዕ ኣቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዕ ኣቡነ ሕርያቆስ
የኣዲስ ኣበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት፣
በኣጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፦
ማሕየዊት በምትሆን ሞቱ ሰማያውያንና ምድራውያንን ያስታረቀ፣ በቅድስት ትንሣኤውም የሙታንን ሕይወት በተስፋ ያለመለመ ጌታችን፣ ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንኳን ለዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“እስመ ተዋለጠ እግዚአብሔር ዓለመ በክርስቶስ ኣናኅስዮ ኃጢኣቶሙ ወኢነጺሮ ጌጋዮሙ፤ ወረሰየ ላዕሌነ ቃለ ሥምረቱ፤ ወወሃበነ መልእክተ ሣህሉ፡- እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን ኣይቈጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል ኣኖረ” (2ቆሮ. 5፥19)።
የእግዚአብሔርም ልጅ፣ የሰውም ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሰብእነት ሲገለጽ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ እንደነበረው ቅዱስ መጽሓፍ ይነግረናል፤ እሱም በሰማይም፣ በምድርም ያሉትን በሙሉ ማስታረቅ፣ ማገናኘትና ኣንድ ማድረግ ነበረ፤
ጌታችን ይህንን ሲያደርግ ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን የለያየው ምክንያት በማስወገድ ነው፤ የመለያየቱ ምክንያት ክፉ ኅሊና ኣምጦ የወለደው በደልና እሱን ተከትሎ የተከሠተው ኃጢኣት ነበረ፤ በኃጢኣት ምክንያት የገባው ሞት ደግሞ የቅጣቱ ማሳያ ፍርድ ነበረ።
የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በፈጸሙት ስሕተት መነሻነት ምድርንና ምድራውያንን ለከባድ ቅጣትና መርገም የዳረገው ይህ መለያየት ለሰማያውያኑም ተርፎኣል፤
ምክንያቱም መለያየቱ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በመላእክትና በሰው፣ በሰውና በሰው፣ በነፍስና በሥጋ ጭምር የጥል ግድግዳን ገንብቶ እስከ ክርስቶስ ዕለተ ስቅለት መዝለቁን በቅዱስ መጽሓፍ የምናውቀው ስለሆነ ማለት ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!

ቀዳማዊና ዘላለማዊ የሆነው ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብእናችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም የተገለጸው ሰማያውያንንና ምድራውያንን የለያየው የጥል ግድግዳን ለማፈራረስ ነው፤
ለመለያየት ምክንያት የሆነችውን ኃጢኣት በሰውነቱ በመቅጣት የሕግን ትእዛዝ ከፈጸመ በኋላ የዕርቁን ተግባር በወሳኝ መልኩ ኣከናውኖታል፤
በክርስቶስ ቤዛነት የሆነው ይህ ዕርቅ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደደ ነበረና እሱ ራሱ በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ኣስታረቀ፤
ለዚህም ነው ተበዳይ እሱ፣ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው እሱ፣ ኣስታራቂ እሱ፣ ታራቂ እሱ ሆኖ የምናገኘው፤ ለሱ የሚሳነው ነገር የለምና ለኛ ግር የሚል ቢመስልም ለሱ ቀላል ነበረ።
በዚህ የዕርቅ ተግባር ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሰውና ሰው፣ ነፍስና ሥጋ ታርቀው በይፋ ተገናኙ፤ በኅብረትና በኣንድነትም መኖር ቻሉ፤ በቀኙ ለተሰቀለው ሽፍታ “ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” የሚለው ቃለ ምሕረትና “ኣባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ ኣደራ እሰጣለሁ” የሚለው ቃለ ኣማሕፅኖ የዕርቁ፣ የግንኙነቱና የኣንድነቱ ማሳያ ኣስረጅ ናቸው።
ስቅለተ ክርስቶስ ነፍሶቻችን ወደ ግዞት ቤት ሳይሆን ወደ ገነት እንዲገቡ፣ የሚቀበላቸውም ራሱ እግዚአብሔር እንዲሆን ያስቻለ ታላቅ መለኮታዊ ፍጻሜ ነው፤
እኛ “ክርስቶስ መድኃኒታችን ነው፤ ኣድኖናል” ብለን በልበ ሙሉነት የምንመሰክረው፣ እሱም “ሰላሜን ሰጠኋችሁ” ብሎ የሚያረጋጋን በመሰቀሉ ይህንን ውጤት ስላስገኘልን ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
የድኅነታችንና የሰላማችን መሠረት የሆኑትን የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለዓለም ማኅበረ ሰብ የማብሰርና የማሥረጽ ተግባር የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቍጥር ኣንድ ተልእኮ ነው፤
ነገረ ሞቱና ነገረ ትንሣኤው በኣስተውሎት፣ በጥልቀትና በተመሥጦ ስናስተምር በውስጡ የምናገኘው የዕርቅ፣ የሰላምና የኣንድነት ምስጢር ነው፤
እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ የክርስቶስ መልእክተኞች እንደ ቃሉ ራሳችንን ክደን በሚጠበቀው መጠን ተልእኮኣችንን መወጣት ብንችል ኖሮ፣ ኣሁን በዓለማችን የተፈጠረው መለያየትና ግጭት ኣይኖርም ነበር፤
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባንችልም በእጅጉ መቀነስና ዓቅሙን ማዳከም እንችል ነበር፤ ነገር ግን ተልእኮኣችንን በኣግባቡ ኣለመወጣት ኣንድ ነገር ሆኖ የዓለሙ መሳሪያ ሆነን መገኘታችን “በዕንቅርት ላይ…” ሆኖ ይስተዋላል።
ይሁንና ኣሁንም ሕዝቡን ወደ ኣንድነት፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ ሰላም፣ ወደ ዘላቂ የጋራ ጥቅምና ወደ ፈሪሐ እግዚአብሔር ማምጣት የጉባኤያችን ዓቢይ ተግባር ሊሆን ይገባል፤ እነዚህ ካሉ የምናጣውም ሆነ የሚያመልጠን የለምና ነው፤
ሃገርን በኃላፊነት ተረክባችሁ በላዕላዊ፣ በማእከላዊና በታሕታዊ መዋቅር የምትገኙ፣ እንደዚሁም ኣማራጭ ሓሳብ ኣለን ብላችሁ የምትንቀሳቀሱ ልኂቃነ ሃገር ፣ ሁላችሁም እግዚአብሔርን ከሚያውቅ፣ ከሚያመልክና ከሚፈራ ሕዝብ የተገኛችሁ ናችሁና በልባችሁ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ድምፁንም ስሙ፤ የሱ ገንዘብ በሆኑ ፍጡራንም ኣትጨክኑ፤ ሰውን መያዝ የሚቻለው ኅሊናን በመርታት እንጂ በሌላ ኣይደለምና፣
የሕዝቡን ፍላጎትና የልብ ትርታ በሚገባ ኣዳምጡ፤ ሕዝቡ የሚፈልገው በኣንድነትና በእኩልነት መኖር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ፍትሕን ማስፈን፣ ለኑሮው የሚበቃ ምጣኔ ሃብትን ማግኘት፣ የእምነት ነጻነትና እኩልነት መረጋገጥ የመሳሰሉት ናቸው።
ሕዝቡ እነዚህ ከተሟሉለት ተደመጠ ማለት ነው፤ ከተደመጠ ደግሞ እሱም በበኩሉ ያደምጣል፤ ይከተላልም፤
ስለሆነም ለሁሉም ልጆቻችንና ወገኖቻችን የምናስተላልፈው ወቅታዊ ጥሪ ሁሉንም ችግሮቻችን በሰላምና በሰላም ብቻ ለመፍታት ተባበሩ የሚል ነው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረገው ኣማራጭ ሁሉ ለዘላቂ ሰላማችን ኣይበጅም እንላለን።
በመጨረሻም፦
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ ኣምስተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለመላው ኢትዮጵያውያን እናበስራለን!!!
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሓት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘኣኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
ኣዲስ ኣበባ – ኢትዮጵያ



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1