#Ethiopia | የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የአርሲ ኦሮሞን ጥልቅ ባህል፣ ታሪክና ማህበራዊ እሴቶች መሰረት ያደረገ “ሰዴታ” የተሰኘ አዲስ ትውፊታዊ ቴአትር ለምርቃት ማብቃቱን በዛሬው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
በአፋን ኦሮሞ ተፅፎ የተዘጋጀው ይህ ጥበባዊ ስራ የኦሮሞ ህዝብ ያለውን የቀደመ ስልጣኔና ማህበራዊ ትስስር በሚያንጸባርቅ መልኩ የተቃኘ ሲሆን፣ በተለይም የገዳ ስርዓት ውስጥ የሴቶችን የላቀ ሚና፣ ክብርና ውሳኔ ሰጪነት ለተመልካች ያቀርባል።
ይህ በደራሲ የውብዳር መለያ ተፅፎ በዳይሬክተር ይድነቃቸው ወርቁ የተዘጋጀው ቴአትር፣ በኦሮሞ ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የ”ሲንቄ”ን አይነተኛ ፋይዳ ማለትም እርቅን በማውረድ፣ ሰላምን በማስፈንና የሴቶችን መብት በማስከበር ረገድ ያለውን የማይተካ አቅም በጉልህ የሚያሳይ ነው።
ቴአትሩ ዘመናዊ የመድረክ አቀራረብን ከጥንታዊው ትውፊት ጋር አዋህዶ የያዘ ሲሆን፣ በውስጡም ትውፊታዊ ሙዚቃዎችን፣ አልባሳትንና የቋንቋ ውበትን አጣምሮ በመያዝ ለአንድ ሰዓት ከ40 ደቂቃ ያህል በመድረክ ላይ የሚቆይ ይሆናል።
የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ይህንን ስራ ለተመልካች ማቅረቡ የሀገራችንን የጥበብ ዘርፍ ለማሳደግና የወል ትርክትን ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጾ፣ ስራው በአፋን ኦሮሞ ለሚዘጋጁ የቴአትር ስራዎች አዲስ የጥበብ መንገድ ይከፍታል ተብሎ ይታመናል።
በመሆኑም መላው የጥበብ አፍቃሪዎች፣ የባህል ተመራማሪዎችና የቴአትር ወዳጆች እሁድ ግንቦት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመገኘት የዚህ ታሪካዊና ባህላዊ ስራ ምርቃት ላይ እንዲታደሙ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ጥሪ ቀርቧል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.