የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ሕገ-ወጥ ነው በሚል ውድቅ አድርጎት የነበረውና የምርጫው ሕገ-ወጥነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ፀንቶ የ…

- Advertisement -
Sidebar AD
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ሕገ-ወጥ ነው በሚል ውድቅ አድርጎት የነበረውና የምርጫው ሕገ-ወጥነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ፀንቶ የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን  የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ ትናንት መርጧል። በህወሓት ውሳኔ፣ ከስድስት ዓመት በፊት የተቋቋመው የክልሉ ምክር ቤት ወደ ሥራ መመለሱን የሚነቅፉ አስተያየቶች ከልዩ ልዩ አካላት እየተሰሙ ነው።
በጉዳዩ ላይ ዶቼ ቬለ አስተያየት የጠየቃቸው አንድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኝ፣ «የህወሓት ውሳኔ የፕሪቶሪያውን ግጭት የማቆም ስምምነት ያፈረሰ ነው» ብለዋል። ተንታኙ አክለውም፣ የፌዴራል መንግሥቱ እና ሌሎች ሦስተኛ አካላት ውዝግቡን በሰላም ካልቋጩት፣ በሂደት ግጭት ሊከሰት እንደሚችል አመልክተዋል።
ይህን የህወሓት ውሳኔ ከስምረት እስከ ትዴፓ መሪዎች እና ሌሎችም አካላት ተችተዋል። ውጤቱም አደጋ ያዘለ እንደሚሆን በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።
ስለጉዳዩ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት AFP ያነጋገራቸው ተንታኞችም ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የትግራይ ክልልን መልሶ ለመቆጣጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር አደገኛ ወደሆነ አስከፊ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል አስጠነቅቀዋል ።
በኖርዌይ የኦስሎ ኒው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የክልል ጉዳዮች አዋቂ ክጄቲል ትሮንቮል እርምጃው «እጅግ አሳሳቢ» መሆኑን ገልጸው  «ድርድር ወይ ግጭት ያስከትል አያስከትል ግልጽ አይደለም» ብለዋል።  ሌላው AFP ያነጋገራቸው በቻተም ሀውስ ተንታኝ አቤል አባተ ደምሴ ደግሞ አንድ ግብ ለማሳካት በተደጋጋሚ የሚደረግ ተጽእኖ በቀላሉ ወደ አስከፊ ግጭት ሊያመራ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል ።
በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከህወሓት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ማብራሪያ ለመጠየቅ ዶቼቬለ ጥረት ቢያደርግም ምላሽ አላገኘንም። የፌዴራል መንግሥት ስለጉዳዩ እስካሁን በይፋ  ያለው ነገርም የለም። (DW)
@seledadotio
@seledadotio

Source: SeledaPost

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1