ዲኬ ሆልዲንግስ የሀገር ውስጥ ምርትን የሚያበረታቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አስተዋወቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​ዳግም ኬኔዲ (ዲኬ) ሆልዲንግስ በኢትዮጵያ ታምርት ባዛር ላይ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን የሚያሳዩና የውጭ ምንዛሬን የሚተኩ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለጎብኚዎች አቅርቧል።

ኩባንያው በተለይም በግብርና፣ በኢነርጂ እና በከተማ ውበት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ውጤቶቹን በማሳየት ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በኤግዚቢሽኑ ላይ የተገኙት የኩባንያው የሽያጭና አገልግሎት መሃንዲስ ኢንጂነር ዮናስ ሀይለገብርኤል እንደገለጹት ድርጅቱ ዘንድሮ አዳዲስና ነባር ምርቶቹን ይዞ የቀረበ ሲሆን የቆይታ ጊዜውም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ገልጸዋል።

​በግብርናው ዘርፍ ድርጅቱ ያመረታቸው የዲስክ ሀሮው፣ ሪጀር እና የተለያዩ ባለ ዲስክ ማረሻዎች በስፋት ለእይታ የቀረቡ ሲሆን እነዚህም ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መሆናቸው ተገልጿል። ኢንጂነር ዮናስ እንዳሉት ድርጅቱ 15 ኩንታል እስከ 70 ኩንታል በሰአት መፈልፈል የሚችሉ የበቆሎ መውቂያዎችንና ሁሉንም የሰብል አይነቶች በአንዴ የሚወቁ ማሽኖችን በማቅረብ የገበሬውን ድካም ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል። አቶ ታረቀኝ ይልማ በበኩላቸው ድርጅቱ ትራክተሮችን በመገጣጠም እና ሌሎች የግብርና ግብአቶችን በማምረት የመንግስትን የኢምፖርት ሰብስቲትዩሽን አቅጣጫ እየተከተለ መሆኑን አብራርተዋል።

​ሌላው በባዛሩ ላይ ትኩረት የሳበው የኩባንያው “ስማርት ፖል” ወይም ዘመናዊ የጎዳና መብራት ምሰሶዎች ናቸው። እነዚህ ፖሎች ከመብራትነት ባለፈ የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና እሴት በሚያንጸባርቅ መልኩ የተሰሩ ሲሆን የኦሮሚያን ኦዳ፣ የትግራይን አክሱም ሀውልት እና የአማራን ዋሊያ የመሳሰሉ ምልክቶችን አካትተዋል። ኢንጂነር ዮናስ እንደገለጹት እነዚህ ፖሎች በኮሪደር ልማት ላይ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በጎንደር፣ በሚዛን አማንና በሌሎች ከተሞች ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

​በኢነርጂ ዘርፍም ዲኬ ሆልዲንግስ በደብረ ብርሃን ጫጫ አካባቢ ባለው ፋብሪካው ትራንስፎርመሮችን በማምረት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሰፊው እያቀረበ መሆኑ ተገልጿል። አቶ ታረቀኝ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም 100 ፐርሰንት ከውጭ ይገባ የነበረውን ትራንስፎርመር አሁን በሀገር ውስጥ ስፔስፊኬሽን መሰረት ማምረት ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ ለሆቴሎችና ለኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ የፕላስቲክ ውጤቶችንና የተለያዩ የፋብሪካ ማሽኖችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

​ድርጅቱ “ሚዛን” የተባለ የሀገር ውስጥ የትራክተር ብራንድ በማስተዋወቅ በባሌ፣ ምንጃርና ሞጆ አካባቢዎች ለሚገኙ ገበሬዎች ውጤታማ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ኢንጂነር ዮናስ አክለው ገልጸዋል። እነዚህ ትራክተሮች የሀገሪቱን መልከዓ ምድር ባገናዘበ መልኩ በሄቪ ሻንሲ የተገነቡና ለኦፕሬተሩ ምቾት ሲባል ካሜራና ኤርኮንዲሽን የተገጠመላቸው ናቸው። አቶ ታረቀኝ እንደገለጹት ድርጅቱ በዋጋም ሆነ በጥራት ከውጭ ከሚገቡት ጋር ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን እያቀረበ ይገኛል።

​ዲኬ ሆልዲንግስ በአሁኑ ወቅት ከሁለት መቶ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል የፈጠረ ግዙፍ ተቋም መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ዮናስ፣ በቀጣይም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ምርምርና ዲዛይን ላይ ትኩረት በማድረግ ስራቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል። ድርጅቱ በተለይም በግብርናው ሜካናይዜሽን ላይ ከባንኮች ጋር በመተባበር የክሬዲት ሲስተም በማመቻቸት ለገበሬው ማሽኖችን እያቀረበ ይገኛል። በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ የኢትዮጵያ ታምርት ባዛር ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ትልቅ መድረክ እንደሆነላቸው ገልጸዋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2