የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕዳ 51.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተገለጸ

- Advertisement -
Sidebar AD

​#FastMereja I የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ዕዳ 51.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለፓርላማ አስታወቁ። ሚኒስትሩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ መንግስት ከአሜሪካ ጋር በየዓመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያገኝበትን አዲስ የድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል።

​ከአጠቃላይ ዕዳው ውስጥ 33.5 ቢሊዮን ዶላሩ የውጭ ዕዳ ሲሆን፣ ቀሪው 18.3 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ የሀገር ውስጥ ዕዳ መሆኑ ተጠቁሟል።

22.1 ቢሊዮን ዶላሩ የፌደራል መንግስት፣ 11.5 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ዕዳ ነው።

17.5 ቢሊዮን ዶላሩ የፌደራል መንግስት ሲሆን፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ድርሻ 0.8 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

​የልማት ድርጅቶች ዕዳ ዝቅ ሊል የቻለው በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሠረት ከንግድ ባንክ ተበድረውት የነበረው ዕዳ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር በመዞሩ እንደሆነ ተብራርቷል። ሚኒስትሩ ዕዳው “በጣም ጤናማ” በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የውጭ ዕዳ የመክፈል አቅምም እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።

​በበጀት ዓመቱ ለዕዳ ክፍያ ከተመደበው 463.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 226.5 ቢሊዮን ብር ተከፍሏል። በሌላ በኩል፣ ከውጭ ሀብት አሰባሰብ ረገድ በዘጠኝ ወራት 3.1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 2 ቢሊዮን ዶላር (የዕቅዱን 65.1%) ማሳካት ተችሏል። ከዚህ ውስጥ 914.2 ሚሊዮን ዶላሩ ከዓለም ባንክ የተገኘ ነው።

​አሜሪካ በየዓመቱ የምታደርገውን የ1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ በተመለከተ፣ ስምምነቱ በቅርቡ በካቢኔ እንደሚጸድቅና ይህም ቀደም ሲል ተቋርጦ በነበረው ድጋፍ ምክንያት በጤና፣ ትምህርትና ግብርና ዘርፎች ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ጫና እንደሚያቃልል ተገልጿል።

ዘገባው የሸገር ሬዲዮ ነው።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1