ጠጥተው አውሮፕላን የሚሳፈሩ ተጓዦች ሁከት እየፈጠሩ ነው ተባለ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የአውሮፓው ግዙፍ እና በዝቅተኛ የዋጋ ተመኑ የሚታወቀው ራያንኤር (Ryanair)፣ በበረራ ወቅት የሚፈጠሩ የረብሻ ድርጊቶችን ለመቀነስ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ የሚቀርብ የአልኮል ሽያጭ ላይ “የቆርጥ ቀን” ገደብ እንዲጣል ጥሪ አቀረበ።

​የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማይክል ኦሊሪ፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ የሚታየውን “ያለ ገደብ መጠጣት” ክፉኛ ኮንነዋል። እንደ ኦሊሪ ገለፃ፣ ጉዳዩ አየር መንገዱን ለከፍተኛ ኪሳራና ለደህንነት ስጋት እየዳረገው ይገኛል።

​​አየር መንገዱ በዋናነት የሚከተሉት ህጎች እንዲተገበሩ እየጠየቀ ነው፡-

​-ከጠዋቱ 4 ሰዓት (10 AM) በፊት በአየር ማረፊያ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች ውስጥ ማንኛውም አይነት የአልኮል ሽያጭ እንዲታገዱ።

-​ለአንድ ተሳፋሪ ከሁለት መጠጥ በላይ እንዳይሸጥላቸው።

​-ይህንን ገደብ ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዱ ተሳፋሪ መጠጥ በሚገዛበት ወቅት የመሳይፈሪያ ትኬቱን (Boarding Pass) እንዲያሳይ በማድረግ ሽያጩን መቆጣጠር።

​ማይክል ኦሊሪ እንደሚሉት፣ በቅርብ ጊዜያት በአልኮልና በተለያዩ አደንዛዥ እጾች ተፅዕኖ ስር ሆነው የበረራ ሰራተኞችን የሚያጠቁና ረብሻ የሚፈጥሩ ተሳፋሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

​“በአሁኑ ወቅት በረብሻ ምክንያት በቀን በአማካይ አንድ በረራን አቋርጠን በተለዋጭ አየር ማረፊያ ለማሳረፍ እየተገደድን ነው” ሲሉ የችግሩን ስፋት ገልጸዋል።

​ራያንኤር የአየር ማረፊያ አስተዳዳሪዎችንም ከመወረፍ አልተቆጠበም። አየር ማረፊያዎች የተሳፋሪዎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ፣ ከመጠጥ ሽያጭ የሚገኘውን ትርፍ ብቻ እያሳደዱ ነው ሲል ከሷል።

​ይህ የራያንኤር አቋም በጉዞ ኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ የፈጠረ ሲሆን፣ ተሳፋሪዎች ከጉዞ በፊት ያላቸውን “የመዝናናት ነፃነት” እና የአየር መንገዱን “የደህንነት ስጋት” ያፋጠጠ ሆኗል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #
​#Ryanair #AviationSafety #TravelNews #AirportRules #FlightSafety #MichaelOLeary #የጉዞ_ዜና


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: