መገናኛ ብዙሃን ከጎራተኝነት ወጥተው ለሀገራዊ መግባባት እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች የተገመገሙበት የምክክር መድረክ ትናንት ሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።

በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መገናኛ ብዙሃን ከዋልታ ረገጥነትና ከጽንፈኝነት አስተሳሰብ በመራቅ በእውነት ላይ የተመሰረተ ትርክት የመገንባት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ የኢቢሲ፣ የኢዜአ፣ የኢኘድ፣ የፋና፣ የአዋሽ ኤፍኤም እና የኤን ቢ ሲ ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት የስራ መሪዎች ተገኝተው ከለውጡ ወዲህ በሚዲያ ምህዳሩ ላይ የታዩ ስኬቶችንና ተሞክሮዎችን አጋርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስምንት ዓመታት የሚዲያ ዘርፉን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎች ለሀገር ግንባታ የሚረዳ ጠንካራ መሰረት መጣላቸውን ገልጸው፣ ይህ ውጤት እንዲቀጥል ተቋማቱ ለጋራ ማንነትና ለብሔራዊ መግባባት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ይዘቶቻቸውን በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በጥናት በመደገፍ ጥልቅ ትንተና ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ከውጫዊ የአርዕስት ሽያጭና ተራ መረጃዎች ባለፈ ለሀገር አጀንዳዎች ትኩረት እንዲሰጡ፣ ሙያዊ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉና ለህዝብ ቅርብ በመሆን ሚዛናዊ ዘገባዎችን እንዲያቀርቡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጋዜጠኞች ስለሚዘግቡት ጉዳይ፣ ስለ አካባቢው ማህበረሰብ ባህልና አኗኗር በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እውነት ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም እንኳን ለእውነት በመቆም ለሀገር ብልጽግና መንገድ ጠራጊና ችግር ፈቺ ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#ሚዲያ #ኢትዮጵያ #ዐቢይአሕመድ #ሀገራዊትርክት #መገናኛብዙሃን #ብሔራዊመግባባት #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2