“ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም።
በህግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ።” ይላል ታላቁ ሊቅ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡
አባቷ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር 86÷1-7 ግንቦት አንድ ቀን በሊባኖስ ተራራ የተወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን “መሠረቶችዋ በተቀደሱ ተራሮች ላይ ናቸው፡፡” በማለት አስቀድሞ ትንቢት ተናግሮላታል፡፡ “የተቀደሱ ተራሮች” ያለውም የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ክህነት ከሆኑት ከተቀደሱት ከኢያቄምና ከሐና የመሆኑን ምስጢር ሲያመለክት ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ትንቢቱንና የእመቤታችንን የትውልድ ሀረግ አስማምታ “እመቤታችን በአባቷ ከንጉሡ ከዳዊት፤ በእናቷም ከካህኑ ከአሮን ወገን ነው” ብላ ታስተምራለች፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ “ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል፡፡” በማለት በምዕራፍ 11÷1 ይናገራል፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ልደት ከሰው ሁሉ ልደት ይልቅ የከበረ ለአምላክ ሰው መሆን፣ ለተስፋው ቃል መፈጸም መንገድ የጠረገ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ከነገደ ዕሴይ እንደሚሆንና እርሷም አበባ የተባለ አካላዊ ቃል ክርስቶስን በሕቱም ድንግልና እንደምትወልድ ተገልጾለት የተናገረው ከአበይት ነቢያት አንዱ ኢሳይያስ “ከዕሴይ ስር ትወጣለች” ያላት አበባን የምታስገኝ በትር፣ አምላክ ሰው የሆነባት፣ ድንቅ የተዋሕዶ ምሥጢር የተፈጸመባት፣ በግንቦት አንድ ቀን የተወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የእመቤታችን ወላጆች ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷ ቅዱስ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች እናቷ ቅድስት ሐና ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ። በጊዜው ካህናቱ የመካኖችን መብዓ አይቀበሉም ነበርና፣ ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘን እንዲያርቅላቸው በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽመው ይማልዱ ነበር፡፡
የለመኑትን የማይነሳ አምላክም የልባቸውን መሻት ተመለከተ፡፡ ክቡር አባታችን ቅዱስ ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቆሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው፡፡ በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው በመውረድ የመልአኩን ብስራት ለቅድስት ሐና ነገራት። እርሷም ቃሉ እውነት እንደሆነ አመነች። ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገነች፤ ሴትም ወንድም ብትወልድ በዘመናቸው ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ልታደርግ ስዕለት ተሳለች፡፡ እናታችን ቅድስት ሐና የመጽነሷ ነገር ሲሰማም ቤተ ዘመዶቿ መጥተው ጎበኗት፡፡ አንድ አይኗ የማያይ ዘመድ ነበረቻት፣ “ሐና እግዚአብሔር ያደረገልሽ ይህ ድንቅ ነገር ምንድነው?” ብላ ማሕጸኗን በዳሰሰችበት እጇ አይኗን ብትነካው በርቶላታል፡፡
ይህን አብነት አድርገው ሕሙማን እየመጡ ይፈወሱ ነበር፡፡ አይሁድም ለምቀኝነት አያርፉምና የእነዚህ ወገን ዳዊትና ሰሎሞን አርባ፣ አርባ ቀጥቅጠው ገዙን አሁን ደግሞ ከዚህች የሚወለድ ሊገዛን ነውን? በድንጋይ ወግረን እንግደላት ብለው ተነሱ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም ኢያቄምን ወደ ሊባኖስ ተራራ ይዘሀት ሽሽ ብሎት በዚያ ሳሉ ግንቦት 1 ቀን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳለች፡፡ በድንጋጤና በጥድፊያ ሲወጣ ከያዘው ስንዴ በስተቀር የሚያቀርብላት ምግብ አልነበረውምና ንፍሮ ቀቅሎ፣ ቂጣ ጋግሮ አቅርቦላታል፡፡
በልደታ ቀን ንፍሮና ቂጣ የምንበላው ይህን አብነት አድርገን ነው፡፡ ገዳማውያን ዓለምን ትተው፣ ከምግብ ርቀው ለነፍሳቸው ሲገዙ እርሷን ተስፋ አድርገው ነውና ጸሎታቸውን ፈጥና ታሳርጋለች፡፡ ምልጃዋ ሕይወትን በሚያሰጥ በቅድስት ድንግል ማርያም ሥም ገዳማውያኑን እንደግፍ በዓታቸውንም እናጽና፡፡ ከበረከትቷ እንካፈል፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957
Source: FastMereja









No comments yet.